የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተከናወኑ ስራዎች አበረታች ናቸው...ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደ ማሪያም

95

ፍቼ ፤የካቲት 29/2013(ኢዜአ) ፡- በተለያዩ መስኮች የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተከናወኑ ስራዎች አበረታች መሆናቸውን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በሚኒስትር ማዕረግ የማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደ ማሪያም ገለጹ።

"የሴቶችን መብት የሚያከብር ማህበረሰብ እንገንባ" በሚል መሪ ሃሳብ አለም አቀፍ የሴቶች ቀን  ዛሬ በሰላሌ ዩኒቨርሲቲ  በውይይት ተከብሯል።

በዝግጅቱ ላይ የተገኙት ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደ ማሪያም  እንደገለጹት፤ በትምህርት ፣ ጤናና ሌሎችም የልማት መስኮች የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ  የተከናወኑ ስራዎችና ተገኙ ውጤቶች አበረታች ናቸው።

ሆኖም ከችግሩ ስፋት አንፃር አሁንም ብዙ መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

"የሴቶች ችግር ሊፈታ የሚችለው ከሁሉ በፊት ሴቶች የነቃ ተሳትፎ ሲደርጉ   ነው ያሉት ፕሮፌሰር ሂሩት ለዚህም ከተናጠል  ይልቅ ተደራጅቶ መንቀሳቀስ ለውጤት የሚያበቃ መሆኑን አስረድተዋል።

የሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ገናናው ጎፌ በበኩላቸው በሀገሪቱ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ሴቶች ተጠቃሚና ተሳታፊ እንዲሆኑ ዩኒቨርሲቲው ፖሊሲና ሰትራቴጂ ቀርፆ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ ዝቅተኛ ሽፋን ያለውን የሴት መምህራን ቁጥር ማሳደግ ፣ በምርምርና ስርፀት ያለውን ተሳትፎ ከፍ ከማድረግ በተጨማሪ ሴቶችን ወደ አመራር ለማውጣት የሙያ ክህሎት በማላበስ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችሉ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ እንደሚገኙ አብራርተዋል።

የሴቶችን ተሳታፊነትና እኩል ተጠቃሚነት   ለማረጋገጥ ከሴቶች አደረጃጀት ጋር አቅዶ መንቀሳቀስ እንደሚገባ የተናገሩት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው የሴቶች፣  ህፃናትና ወጣቶች ዳይሬክተር ወይዘሮ ሃና ታምሩ ናቸው።

ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ ወይዘሮ ማስረሻ ገብረወልድ በሰጡት አስተያየት ሴቶች በተባበረ ክንድ ያለ እድሜ ጋብቻን፣  አስገድዶ መድፈርንና ሌሎችን ጥቃቶች ለማስቆም መታገል እንዳለባቸው አመልክተዋል።

በውይይቱ ሴቶችን እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ትምህርት ከመስጠት በተጨማሪ ችግሮችን ለመፍታት  የሚረዱ ምክረ ሃሳቦች ተነስተዋል።

የሴቶች ትግልና ታሪክ በሚዘክር ውይይት  በተከበረው በዓል  ከዞኑና  ፍቼ ከተማ የተውጣጡ  አመራሮች፣ ተማሪዎችና መምህራን ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች  ተሳትፈዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም