በመጪው ምርጫ ኢትዮጵያዊነት አሸናፊ ይሆናል ... ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ

69

የካቲት 28 /2013 (ኢዜአ) ''መጪው ምርጫ ለኢትዮጵያ ብልፅግና ተግቶ የሚሰራና የኢትዮጵያን አሸናፊነት የሚያረጋግጥ ሰላማዊ ምርጫ ሆኖ ይከናወናል'' ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ከዱር ቤቴ ገንዳ ውሃ የሚገነባውን የኮንክሪት አስፋልት መንገድ ባስጀመሩበት ወቅት ''እኛ የምንፈልገው ኢትዮጵያ አሸናፊ እንድትሆን ነው'' ብለዋል።

መጪው ምርጫ ሰላማዊ ሆኖ ሁሉም ተፎካካሪ ሃይሎች እኩል የሚወዳደሩበት መድረክ የፈጠረ እንደሚሆን ተናግረዋል።

"የላቀ ሃሳብ፣ ተግባርና ልምድ ያለው ቃል መግባት ብቻ ሳይሆን ሰርቶ ማሳየት የፈለገ ህዝቡን የሚያዳምጥና የሚያከብር አሸናፊ ሊሆን ይገባል” ያሉት ዶክተር ዐቢይ፤ የማይሰርቅና ለኢትዮጵያ የሚተጋ ሰው ተለይቶ አደራውን የሚረከብበትን መንገድ የሚፈጥር ምርጫ እንደሚከናወንም ገልጸዋል።

''በዚህ ምርጫ ህዝቡ ያሻውን ይምረጥ'' ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለምርጫው ሰላምን በማስቀደም እኩል የመወዳደሪያ መድረክ እንደሚኖር ተናግረዋል።“በ6ኛው አገራዊ ምርጫ ለኢትዮጵያ የቀና አገለግላለሁ የሚል አካል መብት የሚያገኝበት ምርጫ እንዲሆን እንፈልጋለን” ብለዋል።

ብልፅግና ፓርቲ ለምርጫው ፍትሃዊነትና ስኬታማነት ሃላፊነቱን እንደሚወጣ ጠቁመው፤ “ከሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በመስራት ኢትዮጵያን ወደ ሚፈለገው የብልፅግና ማማ ለማውጣት ቀን ከሌት እንሰራለን” ሲሉም ተናግረዋል።

''ለእኛ ህልማችን፣ ደስታችን፣ ሰቀቀናችን፣ ተድላችን፣ ብርታታችን፣ እረፍታችንና ሰላማችን ኢትዮጵያና ኢትዮጵያ ብቻ ናት'' ሲሉም አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ በነፃነት ለጥቁር ህዝቦች አርአያ እንደሆነች ሁሉ በብልፅግናና በልማትም ፍላጎቷን እንድታሳካ በመከባበር ስሜት በጋራ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም