ኮሌጁ የስርዓተ ትምህርት ክለሳ እያደረገ ነው

107

አዲስ አበባ፣ የካቲት 27/2013 ( ኢዜአ) የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ለተማሪዎች የሚሰጠውን የትምህርት ጥራት ለማሻሻል የሚረዳ የስርዓተ ትምህርት ክለሳ እያካሄደ መሆኑን ገለጸ።

ኮሌጁ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተመሰረተበትን 70ኛ ዓመት በተለያዩ ዝግጅቶች አክብሯል።

በበዓሉ አከባበር ላይ የኮሌጁ መምህራንና የቀድሞ ተማሪዎች የታደሙ ሲሆን "ኮሌጁ ከየት ተነስቶ የት ደረሰ፤ በቀጣይ ምን ላይ ያተኩራል" የሚል ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል።

የኮሌጁ ዲን ዶክተር ዓለሙ መኮንን እንደገለጹት ኮሌጁ ለተማሪዎች የሚሰጠውን ትምህርት ጥራት ለማሻሻል የስርዓተ ትምህርት ክለሳ እያካሄደ ነው።

የክለሳ ሥራው እየተጠናቀቀ መሆኑንና ከዚህ በፊት ሦስት ዓመት የነበረው የተማሪዎች የቆይታ ጊዜ በክለሳው ወደ አራት ዓመት ከፍ የሚል መሆኑን ጠቁመዋል።

በዚህም የቅድመ መደበኛ ተማሪዎች በመጀመሪያው ዓመት የትምህርት ዘመን እውቀታቸውን የሚያሰፉ የተለያዩ እውቀቶች እንዲያገኙ በስርዓተ ትምህርት ክለሳው ውስጥ እንዲካተቱ መደረጉን ገልፀዋል።

ዶክተር ዓለሙ እንዳሉት በኮሌጁ የሚሰጡ ትምህርቶች ጥራት ከፍ እንዲል የተለያዩ እርምጃዎች እየተወሰዱ ያሉት በአገር አቀፍ ደረጃ በቅርቡ የተዘጋጀውን የትምህርት ፍኖተ ካርታ መሰረት በማድረግ ነው።

በተለይም የቅድመ መደበኛ ተማሪዎች ወደ ኮሌጁ ከመግባታቸው በፊት ተገቢውን እውቀት መጨበጣቸውን ለመለየት ፈተና ወስደው እንዲገቡ የማድረግ ዕቅድ እንዳለም አክለዋል።

የኮሌጁ ተማሪዎች በንድፈ ሀሳብ የቀሰሙትን እውቀት በተግባር እንዲያዳብሩ ከኢንዱስትሪዎችና ከተቋማት ጋር በመተባበር ተግባራዊ እውቀት እንዲጨብጡ ማድረግ ሌላው በክለሳው ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ነው ብለዋል።

"በድህረ ምረቃ ዘርፍ ተማሪዎች በኮሌጁ ከመመዝገባቸው በፊት የተለየ ፈተና እንዲወስዱ ይደረጋል" ያሉት ዶክተር ዓለሙ፤ የመመረቂያ ጸሁፍ ጥራትን ለማረጋገጥ ቀደም ሲል በሌላ ሰው ያልተሰራ መሆኑን በኮምፒዩተር ማረጋገጥ የሚቻልበት ስርዓት መዘርጋቱን ጠቁመዋል።

ኮሌጁ ካሉት መምህራን አንጻር በጥናትና ምርምር ዘርፍ የሚጠበቀው ደረጃ ላይ እንዳልሆነ ጠቁመው፤  በቀጣይ በምርምር መስክ ያለውን አፈጻጸም ለማሻሻል በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ኮሌጁ በኢኮኖሚክስ፣ በማኔጅመንት፣ በአካውንቲንግና ፋይናንስ፣ በሎጂስቲክስና ሰፕላይ ቼይን ማኔጅመንት እንዲሁም በሌሎች የትምህርት ዓይነቶች ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ ይገኛል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን የምስረታ በዓል ለማክበር የታደሙ የኮሌጁ መምህራንና የቀድሞ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ደም ለግሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም