የሆቴልና ቱሪዝም ስራ ማሰልጠኛ ማዕከል ያሰለጠናቸውን 425 ተማሪዎችን አስመረቀ

168

አዲስ አበባ፣ የካቲት 27 /2013 (ኢዜአ) የሆቴልና ቱሪዝም ስራ ማሰልጠኛ ማዕከል በተለያዩ የትምህርት ዘርፍ ያሰለጠናቸውን 425 ተማሪዎችን አስመረቀ።

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው ባስተላለፉት መልዕክት “አስቸጋሪውን የኮቪድ-19 ወቅት በማለፍ ለምርቃት በመብቃታችሁ ተማሪዎችን እና የተቋሙ ሰራተኞች እንኳን ደስ አላችሁ” ብለዋል።

ተመራቂዎች ከባለሙያነት ባለፈ የአገር አምባሳደሮች በመሆናቸው በሃላፊነት መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ቱሪዝም ለአገር ኢኮኖሚ ያለውን ፋይዳ ተግባራዊ ለማድረግ ከተመራቂዎች ብዙ ስለሚጠበቅ በትጋት መስራት እንዳለባችው ተናግረዋል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፍወርቅ ካሱ በበኩላቸው ትምህርትን በተገቢው መንገድ ተግባራዊ ማድረግ ከተመራቂ ተማሪዎች እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

“መንግስት እና ህዝብ የሰጣችሁን ሀላፊነት በመወጣት ከዘርፉ የሚገኘውን ፋይዳ አገራችን እንድታገኝ የዜግነት ግዴታቸሁን ተወጡ” ሲሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

የሆቴልና ቱሪዝም ስራ ማሰልጠኛ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ አስቴር ዳዊት የዘንድሮ ተመራቂዎች ከፍተኛ ቁጥርና ውጤት ያላቸው ሴቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።

ተመራቂዎቹ የኮቪድ-19 ፈተናን ተጋፍጠው ለዚህ ስኬት መብቃታቸው የሚያስመሰግናቸው እንደሆነ ተናግረዋል።

በዘንድሮ መርሀ ግብር በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ በዲግሪ 16፣ በደረጃ 3 በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ 202፣ በደረጃ 4 በሆቴል እና ቱሪዝም 157 እንዲሁም በደረጃ 5 በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ 53 ተማሪዎች የተመረቁ ሲሆን በአጠቃላይ 425 ተማሪዎች ለምረቃ በቅተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም