ውብ እና ፅዱ አዲስ አበባን ማየት እፈልጋለሁ፣ከተማዬን እወዳታለው የሚል ሁሉ ለፅዳትዋ መትጋት አለበት - ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ

111

አዲስ አበባ፣ የካቲት 27 / 2013 (ኢዜአ) “ውብ እና ፅዱ አዲስ አበባን ማየት እፈልጋለሁ፣ ከተማዬን እወዳታለው የሚል ሁሉ ለፅዳትዋ መትጋት አለበት” ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እና በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የማዘጋጃ ቤታዊ ዘርፍ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነ በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ንግድ ማተሚያ ቤት አካባቢ በመገኘት “አካባቢዬን በማጽዳት ለከተማዬ ጽዳትና ውበት አምባሳደር ነኝ!” በሚል መሪ ቃል በከተማዋ 25 ሺህ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ የሚሆኑበትን የጽዳት ዘመቻ በይፋ አስጀምረዋል፡፡

ምክትል ከንቲባዋ “ከግላችን ጀምረን አካባቢን ማጽዳት ባህል ሆኖ ለውጥ እንዲመጣ ሁሉም የራሱን ድርሻ መወጣት አለበት” ብለዋል፡፡

ህብረተሰቡ ከተማዋን ባለማቆሸሽ እና በማፅዳት ውብ እና ጽዱ አዲስ አበባን ማየት እፈልጋለሁ፣ከተማዬን እወዳታለው የሚል ሁሉ ለጽዳትዋ መትጋት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የማዘጋጃ ቤታዊ ዘርፍ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነ በበኩላቸው ለተከታታይ ሁለት ወራት በሚካሄደው በዚህ የጽዳት ዘመቻ በሁሉም መንግስት መስሪያ ቤቶች፣ በትምህርት ቤቶች፣ በጋራ መኖሪያ ቤቶች፣ በሃይማኖት እና ልዩ ልዩ ተቋማት ሰራተኞችን እና ነዋሪዎችን በማሳተፍ የጽዳት ስራው እንደሚካሄድ ተናግረዋል።

በዛሬው ዕለትም በሁሉም ክፍለ ከተሞች የጽዳት ዘመቻው ስራ በመካሄድ ላይ መሆኑን ገልጸው፤ “ለዚህ የጽዳት ስራ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች የተሰማሩ በተለይ የሃይማኖት አባቶች፣ ታዋቂ አርቲስቶችና ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች በአምባሳደርነት ተሰይመው በመስራት ላይ ይገኛሉ” ብለዋል፡፡

ዛሬ ከማለዳው 12፡00 ጀምሮ በተካሄደው የጽዳት ዘመቻ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ ታዋቂ የኪነጥበብ ባለሙያዎች፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አባላት፣ የጽዳት ሰራተኞች እና ነዋሪዎች ተሳተፊ ሆነዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም