ወጣቶች ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል ተባለ

84

አዲስ አበባ፣ የካቲት 26-2013 ዓም (ኢዜአ) ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ወጣቶች የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ ገለጸ።

ቢሮው "ለምርጫው ሰላማዊነትና እና ዴሞክራሲያዊነት የወጣቶች ሚና ወሳኝ ነው" በሚል መሪ ቃል ዛሬ ከወጣቶች ጋር ተወያይቷል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወጣቶችና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብርሀም ታደሰ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ወጣቶች ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ነው የጠቀሱት፡፡

ከዴሞክራሲ ሥርአት ግንባታ መገለጫዎች አንዱ ምርጫ መሆኑን ጠቁመው፣ ባለፉት ዓመታት በዴሞክራሲ ሥርአት ግንባታ ላይ በነበሩ ጉድለቶች ሳቢያ ምርጫዎች ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ከመሆን አንጻር ክፍተት እንደነበረባቸው ተናግረዋል።

የወጣቱን ተሳትፎ ለማጎልበት ግንዛቤ በመፍጠር በኩል ሰፊ ሥራ መስራት እንደሚገባ ገልጸው፣ ለዚህም የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።

"መጪው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ወጣቶች የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል" ሲሉም አቶ አብርሀም ገልጸዋል።

ወጣቶች በመራጭነት ብቻ ሳይሆን ተመራጭ ከመሆን አኳያ ተሳትፎ ሊያደርጉ እንደሚገባም እንዲሁ።

እንደ ኃላፊው ገለጻ የአገር ሰላም እንዳይደፈርስ ዜጎች በተለይ ወጣቱ ከውሸት መረጃዎች መራቅና እውነቱን መፈተሽ ይኖርበታል፡፡

በመድረኩ ተሳታፊ የነበሩ ወጣቶች በበኩላቸው ለስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ሰላማዊነት የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ወጣት ያለምወርቅ አየለ ወጣቶች በአገሪቱ የዴሞክራሲ ግንባታ ብሎም በምርጫ ያላቸው ተሳትፎ ከወረቀት በዘለለ ወደተግባር በማውረድ በኩል ክፍተቶች እንደነበሩ አስታውሳለች፡፡

"በቀጣይ አገራዊ ምርጫ ይህንን ችግር ለመፍታት ወጣቶች በዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ውስጥ የበኩላችንን ልንወጣ ይገባል" ብላለች።

ወጣቶች በስድተኛው አገራዊ ምርጫ የሚኖራቸው ተሳትፎ በአገሪቱ ላይ ሊያመጣ የሚችለውን አስተዋጽኦ በመገንዘብ በምክንያታዊነት ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባም አስገንዝባለች።

ወጣቷ በቀጣይ አገራዊ ምርጫ ያመነችበትን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ ዝግጁ መሆኗንም ነው የተናገረችው።

ወጣት ሀብታሙ ጋሻው በበኩሉ ባለፉት ጊዜያት በዴሞክራሲ ግንባታ ተሳትፎ ላይ ያለው ሚና ብዙም እንዳልነበረ አስታውሷል።

"ለወጣቶች የተዘጋጀው መድረክ ወጣቱ በምርጫ ላይ ያለውን የተዛባ አመለካከት እንዲቀይር የሚያደርግ በመሆኑ መሰል መድረኮች በቀጣይ ሊዘጋጁ ይገባል" ብሏል፡፡

ቀደም ሲል በተካሄዱ አምስተኛ ምርጫዎች የተስተዋሉ ክፍተቶችና ችግሮችን ወጣቱ ተገንዝቦ በቀጣዩ አገራዊ ምርጫ ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ሊሳተፍ እንደሚገባ አመልክቷል።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ወጣት አበበ ተፈራ "ምርጫው በሰላም እንዲካሄድ እኛ ወጣቶች የሚወሩ የተለያዩ መረጃዎችን እውነተኛ ስለመሆናቸው ማረጋገጥና ምክንያታዊ በመሆን የበኩላችንን ልንወጣ ይገባል" ሲል ተናግሯል፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም