በከተማዋ የሚካሄዱ ሕገወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎችን የመከላከል ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል

534

የካቲት 25 / 2013 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ የሚስተዋሉ ሕገወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎችን የመከላከልና መቆጣጠር ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ።

የከተማዋ ምክር ቤት የስምንተኛ ዓመት የስራ ዘመን ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤውን አካሂዷል።

ጉባኤው በከተማ አስተዳደሩ የ2013 ዓ.ም ግማሽ ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ተወያይቶ አፅድቋል።

ባለፉት ስድስት ወራት የኑሮ ውድነት ጫናን ለመቀነስ በከተማዋ የሸማቾች የምርት አቅርቦትን በአንድ ላይ በማቀራረብ ማቃለል የሚያስችሉ የገበያ ማዕከላትን በማበራከት ሲሰራ መቆየቱ በሪፖርቱ ተመላክቷል።

የገበያ ማዕከላትን በማበራከት በኩል በተሰራው ስራ የላፍቶ አትክልትና ፍራፍሬ የገበያ ማዕከል 14 ዘመናዊ ሼዶችን በመገንባት በውስጡ 556 ሱቆች ተጠናቀው ስራ መጀመራቸው ተገልጿል።

እናቶችና ወጣት ሴቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ያደረገው የፉሪ ሁለገብ የገበያ ማዕከልና የጀሞ የሰብል ምርት የገበያ ማዕከል አምራቹንና ሸማቹን በቀጥታ በማገናኘት ረገድ አስተዋፅኦ ማድረጋቸውና የኑሮ ውድነቱን ለመቀነስ ጉልህ ድርሻ እንዳላቸው ተመላክቷል፡፡

በግማሽ ዓመቱ 66 ሺህ 504 አዲስ የንግድ ፈቃድ ለመስጠት ታቅዶ 60 ሺህ 129 መሰጠቱን፤ ለ248 ሺህ 465 የንግድ ድርጅቶችም የስራ ፈቃድ እድሳት ለመስጠት ታቅዶ የ244 ሺህ 535 መታደሱ ተገልጿል።

የንግድ ስርዓቱን ከህገወጥና ኢ-ፍትሃዊ አመለካከት ተግባር ለማላቀቅ በተሰራው ስራ 155 ሺህ የንግድ ድርጅቶችን የበር ለበር ቁጥጥር ለማድረግ ታቅዶ ከ292 ሺህ በላይ በሚሆኑት ላይ ተተግብሯል ተብሏል።

ያለ ንግድ ፈቃድ በመነገድ፣ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ፤ ምርት በማከማቸትና በመደበቅ የምርት እጥረት በፈጠሩ የንግድ ተቋማት ላይ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱም ተጠቅሷል።

የፀጥታ አካላትን ለማጠናከር 2 ሺህ 674 የደንብ ማስከበር አባላትና 4 ሺህ 300 ምልምል ፖሊሶች መሰልጠናቸው፤ ከእነዚህም መካከል 2 ሺህ 674 የደንብ ማስከበር አባላትና 1 ሺህ 500 ምልምል ፖሊሶች ተመርቀው ወደ ስምሪት መግባታቸው ተገልጿል።

ቀሪዎቹ የፖሊስ አባላት በቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት ተመርቀው ወደ ስምሪት እንደሚገቡም ተብራርቷል።

በከተማዋ የሚስተዋሉ የውሃ አቅርቦትና የትራንስፖርት ችግሮችን ለመፍታትም ፀጥታ ለማስከበር ባለፉት ስድስት ወራት የተከናወኑ ተግባራት አበረታች መሆናቸውን የምክር ቤቱ አባላት አንስተዋል።  

ሆኖም በከተማዋ የሚስተዋለውን የተደራጀ ሌብነት ችግር ለመፍታት አሁንም ማህበረሰቡን ማዕከል ያደረገ ስራ መጠናከር አለበት ብለዋል።

በከተማዋ የኑሮ ውድነት ከጊዜ ወደጊዜ እየተባባሰ መሆኑና ከውጭ የሚገቡ ብቻ ሳይሆን በአገር ውስጥ የሚመረቱ መሰረታዊ የግብርና ምርቶች ላይ የሚስተዋለውን ጭማሪ በተመለከተ ምን እየተሰራ እንደሆነ የምክር ቤቱ አባላት ጠይቀዋል።

ሕገወጥ የንግድ እንቅስቃሴና የኢኮኖሚ አሻጥር መኖሩን፤ ይህንንም ለመፍታት ግብረ ሀይል ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ዣንጥራር አባይ ገልጸዋል።

የግብርና ምርቶችን ዩኒየኖች ለአምራቹ እንዲያቀርቡ እየተሰራ መሆኑንና በህገወጥ ንግድ ላይ የተሰማሩ አካላት ላይ ክትትልና ቀጥጥር እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው የመዲናዋን ሠላም ለማስከበር ኅብረተሰቡ ከፀጥታ አካላት ጋር በትብብር መስራቱን ጠቁመው ይህን ተግባር በማጠናከር የተደራጀ ሌብነትን ለመከላከል ይሰራል ብለዋል።

የኑሮ ውድነቱን ያናረው ምክንያታዊ ያልሆነ ጭማሪ ነው ያሉት ምክትል ከንቲባዋ ይህንንም ለመፍታት ከኅብረተሰቡ ጋር በቅንጅት ይሰራል ብለዋል።

የምርቶች አቅርቦት ማሳደግ ላይ እንደሚሰራና በተለይ የግብርና ምርቶች ላይ የሚስተዋለውን የዋጋ ጭማሪ ለመፍታት የከተማ ግብርና ላይ በማተኮር መሰራት እንዳለበት አመላክተዋል።