ዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰቡን ችግር ለመፍታት የጀመራቸውን ስራዎች ሊያጠናክር ይገባል - ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

97

የካቲት 25 / 2013 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰቡን ችግር ለመፍታት የጀመራቸውን ስራዎች እንዲያጠናክር ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ አሳሰቡ።

ዩኒቨርሲቲው 70ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን አክብሯል።   

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው በአፍሪካ ቀዳሚ  እንደመሆኑ ለአፍሪካዊያን ወንድምና እህቶች የትምህርት እድል በመስጠት ያበረከተው አስተዋጽኦ የሚዘነጋ አይደለም።   

ዩኒቨርሲቲው ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዩኒቨርሲቲ ይባል በነበረበት ወቅት ለአፍሪካ በመሪነት ደረጃ የተቀመጡ ተማሪዎችን ማፍራት መቻሉን በማሳያነት ጠቅሰዋል።   

የምስረታውን 70ኛ ዓመት ሲያከብር ስኬቶችን ብቻ ሳይሆን ጉድለቶቹ ላይ በመስራት ሊሆን እንደሚገባ ጠቁመው የአገሪቷ የትምህርት ሁኔታ በሚጠበቀው ደረጃ ባለመሆኑ ችግሩ ምንድነው፣ መፍትሄውስ የሚለው ላይ የራሱን ሚና እንዲወጣ አሳስበዋል።     

ኢትዮጵያ ለገጠማት ችግር አገራዊ መፍትሄ እንደምትሻ ገልፀው በሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም በማኅበራዊ ዘርፎች ዩኒቨርሲቲው ችግሮችን ለመፍታት የሚያደርገውን ጥረት እንዲያጠናክር አሳስበዋል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ለጥናትና ምርምር የሚሰጠው ትኩረት እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።  

ለዚህም በዓለም አቀፍ ጆርናል ላይ የታተሙ ከሁለት ሺህ በላይ የጥናት ውጤቶችን ማበርከቱን ጠቅሰዋል።  

ተቋሙ የሰለጠነ የሰው ኃይል በማቅረብ ረገድ ትልቅ ስራ መስራቱን አንስተው ከተመሰረተ እስካሁን 250 ሺህ ተማሪዎችን በማስመረቅ የአገር መሪ፣ የኖቤል ሽልማት ያሸነፉ እና በሌሎችም ቦታዎች ውጤታማ ሰዎች ማፍራቱን ገልጸዋል።  

በተለይም በትምህርት ዘርፍ ፖሊሲ በማዘጋጀትና በተለያዩ ደረጃዎች የስርዓተ ትምህርት ቀረጻ ላይ ጉልህ ሚና መጫወቱን አብራርተዋል።  

በምርምር ዘርፍም ለማኅበረሰቡ የሚጠቅሙ ስራዎችን በግብርና፣ በጤናና ማኅበራዊ መስኮች ማካሄዱን ዘርዝረዋል።  

ዩኒቨርሲቲው ለምርምር የሚሰጠው ትኩረት እያደገ መምጣቱንና በዚህም ምክንያት የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ኅብረት አባል ከመሆን ባለፈ የምርምር ዩኒቨርሲቲ እውቅና ተሰጥቶታል ብለዋል።

ከሕክምና ጋር በተያያዘም በጥቁር አንበሳ ሪፈራል ሆስፒታል በየዓመቱ እስከ 100 ሺህ ለሚደርሱ ዜጎች ነጻ ሕክምና እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።   

ፕሮፌሰር ጣሰው እንዳሉት፤ ዩኒቨርሲቲው በስራዎቹ የተሻለ ስኬት ላይ ለመድረስ የአስር ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ አውጥቷል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ገነተ ልዑል የተሰኘውን ቤተ-መንግስታቸውን ከለቀቁ በኋላ  በ1943 ዓ.ም እንደተመሰረተ መረጃዎች ያመላክታሉ።   

ተቋሙ ሲመሰረት 33 ተማሪዎችን የተቀበለ ሲሆን አሁናዊ የቅበላ አቅሙ 50 ሺህ ደርሷል።  

በቅድመ ምረቃ 80 የትምህርት አይነቶች ያሉት ሲሆን በድህረ ምረቃ ደግሞ በ300 የትምህርት አይነቶች በመስተማር ላይ እንደሚገኝ ከዩኒቨርሲቲው የተገኘው መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም