የለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ኢንደስትሪያል ኮምፕሌክስ በድህነት ላይ ለሚደረገው ዘመቻ ትልቁ መብራት ነው"- ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

68

የካቲት 25/2013 (ኢዜአ) በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን እንሳሮ ወረዳ በ2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር የሚገነባው የሲሚንቶ ፋብሪካ በፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠለት።

ፋብሪካው በኢትዮጵያው ኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ እና በቻይና ዌስት ኢንተርናሽናል ድርጅት በሽርክና የሚገነባ ነው።

የ18 ወራት ጊዜ በተያዘለት የመጀመሪያው የግንባታ ምዕራፍ ሶስት ፋብሪካዎች ወደስራ የሚገቡ ሲሆን በቀን 10 ሺህ ቶን ሲሚንቶ፤ በዓመት 30 ሚሊዮን ካሬ ሜትር ጂፕሰም ቦርድ እና በቀን 600 ቶን መስታወት የሚያመርቱ ናቸው፡፡

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ 'ድህነትም ሆነ ሀብታምነት ከፈጣሪ የተሰጠ ስጦታ አይደለም፤

ኢትዮጵያዊያን ድህነትን ከጫንቃችን ላይ አራግፈን መጣል ካልቻልን የሌሎች ተፅዕኖ አይቀርልንም ብለዋል፡፡

የለሚ ፋብሪካ መገንባትም በድህነት ላይ ለሚደረገው ዘመቻ ትልቁ መብራት ነው ብለዋል፡፡

ሁላችንም አንድ የጋራ አገር እንዳለን በመረዳት ለፕሮጀክቱ ስኬታማነት በትብብር መስራት እንደሚገባም አመለክተዋል፡፡

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር በበኩላቸው ከለውጡ በኋላ ሁሉም ክልሎች በመልማት ፀጋቸው ልክ መልማት የሚችሉበት ፍትሃዊ አሰራር ሰፍኗል ብለዋል፡፡ 

"ለውጡ ባይመጣ ኖሮ ይህ ፋብሪካ እዚህ አይገነባም ነበር የት እንደሚሄድም እናውቃለን" ብለዋል፡፡

የአማራ ክልል መንግስት በክልሉ ሠላም በማስፈንና ለባለሃብቶች ምቹ የስራ ከባቢ በመፍጠር ሌት ተቀን እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

በክልሉ ከፍተኛ የሀይል እጥረት መኖሩን የገለጹት አቶ አገኘሁ የፌዴራል መንግስት በአገሪቷ አቅም ልክ የተመጣጠነ የሀይል አቅርቦት ማመቻቸት እንዳለበትም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም