በደቡብ ክልል ከኪራይ ሰብሳቢነትና ብልሹ አሰራር ጋር በተያያዘ ከ460 በላይ ግለሰቦች ላይ እርምጃ ተወሰደ

77

የካቲት 25/2013 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል በመንግስት ቤትና በመሬት አስተዳደር ዝርፊያ እጃቸው አለበት የተባሉ ከ460 በላይ ግለሰቦች ላይ እርምጃ መወሰዱን የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ አስታወቀ።

የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ የዘርፍ መስሪያ ቤቶች ጉባኤ በዲላ ከተማ ተካሂዷል።

የደቡብ ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ የእቅድና በጀት ዳይሪክተር አቶ አወቀ ቢያዝን ለኢዜአ እንዳሉት፤ በክልሉ በሚገኙ 151 ከተሞች የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮችን ለማረም ጥረት እየተደረገ ነው።

በከተሞቹ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ በመንግስት ቤቶችና በመሬት አስተዳደር ዙሪያ ተገቢ ያልሆነ ድርጊት እየተፈጸመ እንደሚገኝ ከተሰጠ ጥቆማ በመነሳት ማጣራት ሲደረግ መቆየቱን ጠቁመዋል።

በዚህም በኪራይ ሰብሳቢነትና በብልሹ አሰራር ውስጥ የተዘፈቁ ከ460 በላይ ግለሰቦች ላይ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱን አስረድተዋል።

የመንግስት ቤት ወደ ግል ስም ያዞሩ ግለሰቦች እንዲሁም የከተማ መሬት በህገ ወጥ መንገድና ከሊዝ አዋጁ ውጭ ያስተላለፉ ባለሙያዎችና አመራሮች እርምጃ ከተወሰደባቸው መካከል እንደሚገኙበት ተናግረዋል።

እርምጃ ከተወሰደባቸው መካከል ስምንት መሀንዲሶች ከስራ ታግደው ጉዳያቸው በህግ እንዲታይ መመራቱንና አስር አመራሮች ደግሞ ከሀላፊነታቸው መነሳታቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።

የቀበሌ ቤቶች በስማቸው ለማዛወር የሞከሩ 300 ግለሰቦችም ቤቶቹን ተነጥቀው ጉዳያቸው በህግ እንዲታይ መደረጉን አመልክተዋል።

በቀሪዎቹም ላይ እንደየ ጥፋታቸው አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ተናግረው፤ "ህገ ወጦች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል" ብለዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ሀላፊ አቶ ተስፋዬ ይገዙ በበኩላቸው በከተሞች የሚስተዋሉ ህገ ወጥ አካሄዶች በፍጥነት መቆም እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በሰላምና ጸጥታ፣ በመሬትና በግንባታ አስተዳደር እንዲሁም በከተማ ውበትና ጽዳት ዙሪያ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን በመፍታት መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን በሁሉም መዋቅር ክትትል እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም