የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች መመሪያ ደንብ ተዘጋጀ

722

አዲስ አበባ፣ የካቲት 24/2013 ( ኢዜአ) የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች መመሪያ ደንብ መዘጋጀቱን ስፖርት ኮሚሽን አስታወቀ።

የስፖርት ደረጃዎች መለኪያ መስፈርት መዘጋጀቱንም ገልጿል።

በኢትዮጵያ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች አስተዳደር አዋጅ በ2004 ዓ.ም ቢወጣም፤ ደንብና መመሪያ ስላልነበረው በሥራ ላይ ማዋል እንዳልተቻለ ይታወቃል። 

የስፖርት ኮሚሽንም ችግሩን ለማስተካከል መመሪያውን በረቂቅ ደረጃ በማዘጋጀት ይፋ አድርጓል።

በ1990 ዓ.ም የወጣው የኢትዮጵያ ስፖርት ፖሊሲ፤ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ማከናወን የዜጎች መብት መሆኑን ይጠቁማል። 

በመሆኑም ኅብረተሰቡ በሚኖርበት፣ በሚማርበትና በሚሰራበት አካባቢ በስፖርት እንቅስቃሴ ተሳታፊ የሚሆንበትን ሁኔታ ለማመቻቸት የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ድርሻ አላቸው።

በኮሚሽኑ የስፖርት ፋሲሊቲ ዳይሬክተር የሆኑት አስመራ ግዛው ለኢዜአ እንደገለፁት ደንቡ የወጣው ለስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች የወጣውን ደረጃ ማስፈፀሚያ መሆኑን ገልፀዋል።

ከሁሉም ክልል የተውጣጡ የሕግና የስፖርት ከፍተኛ ባለሙያዎች ደንቡን ማውጣታቸውን ተናግረዋል።

የማዘውተሪያ ሥፍራዎች እንዴት እንደሚተዳደሩና እንደሚጠበቁ አዋጁን በመከተል እየተሰራ ቢቆይም በመመሪያና በሕግ ማዕቀፍ ማገዝ ስለሚገባ ደንቡ ወቷል ብለዋል።

ማንኛውም የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ዕውቅና ሊሰጣቸው ግድ በመሆኑና ዝርዝር መስፈርት ተዘጋጅቶ መለካት ስላለባቸው ደንቡ ወጥቷል ነው ያሉት። 

የደንቡ መውጣት ለክልሎች፣ ለስፖርት ማኅበራትና ለመንግሥት እንደሚመጠቅምና የስፖርት ልማቱ ወጥ አሰራር እንዲኖረው እንደሚያደርግ አቶ አስመራ ተናግረዋል።

መመሪያውንም ለመተግብር የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን የሕዝብ ሀሳብና ግብዓት ካካተተ በኋላ ለፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በመላክ ሀሳብ አክሎበት ያፀድቀዋል ብለዋል።

በሌላ በኩል የስፖርት መለኪያ መስፈርት ከዚህ በፊት ለማውጣት ቢሞከርም ተግባር ላይ አለመዋሉን አቶ አስመራ ገልፀው ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ መስፈርት ተካትቶ መውጣቱን ገልፀዋል።

በመሆኑም መሥፈርቱን በማሻሻል አሁን ላይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ባገናዘበና በሥራ ላይ ያጋጠሙ ችግሮችን መነሻ በማድረግ መዘጋጀቱን ነው የገለፁት።

መሥፈርቱም የተለያዩ ማዘውተሪያ ሥፍራዎች የተለያዩ ውድድሮች ማዘጋጀት እንዲችሉ ማሟላት ያለባቸውን ዝርዝር ሁኔታ ማስቀመጡን ተናግረዋል ።

የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራ ቁመቱና ወርዱ ስንት መሆን አለበት? ማሟላት የሚገባው ግብዓት ምንድነው የሚለው ቅድሚያ ታይቷል ነው ያሉት።

የመፀዳጃ፣ የመታጠቢያ፣ የመኪና ማቆሚያ፣ የዳኞች፣ የአሰልጣኞች፣ የስፖርተኞች መቀመጫ፣ ቢሮዎችና የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ክፍል በመሥፈርቱ በዋነኝነት ተካተዋል ብለዋል።

የደረጃ መሥፈርቱም ሲወጣ በሰነድ ደረጃ ከተለያዩ ሀገራት የስፖርት ማኅበራት ተሞክሮ መወሰዱን አቶ አስመራ ገልፀዋል።

የእግርኳስና የአትሌቲክስ ስፖርትን በተመለከተም የካፍን፣ የፊፋንና የዓለምአቀፉን አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የስፖርት ደረጃ መሥፈርት ምን ይመስላል? የሚለው መታየቱን ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ 600 የሚሆኑ ሕጋዊ የሰውነት ማረጋገጫ ሊሰጣቸው የተዘጋጁ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች መኖራቸውን ከኮሚሽኑ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።