ትውልዱ ጦር ሜዳ ሳይዘምት በእውቀትና በሙያው ኢትዮጵያን ወደከፍታ ማማ ማውጣት ይችላል – ወጣቶች

315

የካቲት 23/2013 (ኢዜአ) የዛሬው ትውልድ ጦር ሜዳ መዝመት ሳይጠበቅበት በእውቀትና በሙያው ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ ማማ ማውጣት እንደሚችል ኢዜአ ያነጋገራቸው ወጣቶች ገለጹ።

ወጣቱ ከአባቶቹና እናቶቹ የወረሰውን የሥራ ጥበብና ክህሎት ለአገር ልማት ሊጠቀምበት እንደሚገባም ተናግረዋል።

የአድዋ ድል በዓል አከባበር ታዳሚዎቹ ወጣቶች አሁን ያለው ትውልድ ኢትዮጵያን ለመጠበቅ ከ125 ዓመት በፊት እንደነበረው የአድዋ ጦርነት ወደ ጦር ሜዳ መዝመት እንደማያስፈልገው ገልጸዋል።

ወጣቱ ባለው ሙያና እውቀት አገሩን በማገልገል ኢትዮጵያን ከፍ ማድረግ ከቻለ ትልቅ ድል እንዳስመዘገበ ይቆጠራል ነው ያሉት።

ትውልዱ ትልቁን ጀግንነት ማሳየት ያለበት ድህነትን በማጥፋት፣ ኢትዮጵያን በማልማትና በፍቅርና በመተሳሰብ በመኖር እንደሆነም ወጣቶቹ ተናግረዋል።

ወጣቱ አባቶቹና እናቶቹ ያወረሱትን የሥራ ጥበብና እውቀት ለአገር ልማት ሊጠቀምበት እንደሚገባም አመልክተዋል።ትውልዱ በምክንያታዊነትና በሀሳብ ልዕልና የሚያምን በሳል ትውልድ መሆን እንደሚጠበቅበትም ነው የተናገሩት።

እቴጌ ጣይቱ በአድዋ ጦርነት ካሳዩት ጀግንነት በመማር የአሁኖቹ ሴቶች ለኢትዮጵያ እድገት አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ እንደሚገባም አመልክተዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው ወጣቶቹ የኢትዮጵያን ነጻነት ጠብቆ ለማቆየትና ባላቸው ሙያና እውቀት አገራቸውን ለማገልገል ቃል ገብተዋል።

ከግል ጥቅም ይልቅ የኢትዮጵያን ጥቅም እንደሚያስቀድሙና በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እንደማይደራደሩም አረጋግጠዋል።

ዛሬ በዳግማዊ ምኒልክ አደባባይ 125ኛው የአድዋ ድል በዓል ሲከበር ወጣቶች ፉከራ፣ ሽለላ፣ ቀረርቶና የተለያዩ ትርኢቶችን በማሳየት ለበዓሉ ድምቀት ሰጥተውታል።