ኢትዮጵያዊያን ከአድዋ ድል በመማር የአካባቢያቸውንና የአገራቸውን ሠላም በጋራ ሊጠብቁ ይገባል

74

የካቲት 23/2013 ( ኢዜአ) ኢትዮጵያዊያን ከአድዋ ድል አንድነትን በመማር የአካባቢያቸውንና የአገራቸውን ሠላም በጋራ በመጠበቅ ልማትን ሊያፋጥኑ እንደሚገባ ተገለጸ።

125ኛው የአድዋ ድል በዓል በመተከል ዞን ግልገል በለስ ከተማ ተከብሯል።

በበዓሉ ላይ የከተማዋ ነዋሪዎች፣ የምዕራብ ዕዝ ምክትል አዛዥና የመተከል ዞን የተቀናጀ ግብረ ኃይል አባል ብርጋዴር ጄኔራል አለማየሁ ወልዴ፣ የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ጋሻ ዳንግሶ እና የግልግል በለስ ከተማ ከንቲባ አቶ ሀብታሙ ኡባልታ ተገኝተዋል።

የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፉት ብርጋዴር ጄኔራል አለማየሁ የአድዋ ድል አባቶቻችን በዘር፣ በቀለምና በሃይማኖት ሳይከፋፈሉ የአገርን ክብር አስጠብቀው ያቆዩበት መሆኑን አንስተዋል።

አድዋ የኢትዮጵያ ዳር ድንበር እንዳይደፈርና ነፃነቷን ለማረጋገጥ ደምና አጥንታቸውን በመገበር የሕይወት መስዕዋዕትነት የከፈሉበት ድል መሆኑንም አመልክተዋል።

ኢትዮጵያዊያን ከአድዋ ድል አንድነትን በመማር የአካባቢያቸውንና የአገራቸውን ሠላም በመጠበቅ ልማትን ሊያፋጥኑ እንደሚገባም አሳስበዋል።

በተለይም ወጣቱ ትውልድ አገርን ለማዳን ሲባል በዘር፣ በቀለምና በማንነት መከፋፈል እንደሌለበት ከአድዋ ጀግኖች ብዙ ሊማር እንደሚገባ ነው ብርጋዴር ጄኔራል አለማየሁ ያስገነዘቡት።

የመተከል ዞን አስተዳዳሪ አቶ ጋሹ ዳንግሶ በበኩላቸው "የአድዋ ድል ጀግኖች አባቶች ቅኝ ግዛትን አንቀበልም በማለት ለነፃነታቸው የተዋደቁበት፤ በብርቱ ተጋድሎና መስዋዕትነት ለአፍሪካዊያን ጭምር ኩራት የሆነ ድል ያስመዘገቡበት ነው" ብለዋል።  

ትውልዱ እንደ ቀድሞ አባቶቹ አንድነቱን አጥብቆና ራሱን ከአገር በታች አድርጎ ዘመኑ ለሚጠይቀው ትግል መዘጋጀትና ድል ማድረግ እንዳለበትም አመልክተዋል።

"የአደዋ ድል እኛ ኢትዮጵያዊያን በጋራ ከቆምን የማናሸንፈው ነገር እንደሌለ ጥሩ ማሳያ ነው" ሲሉም ነው የገለጹት።

ለመላው ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ተምሳሌት ሆኖ የሚታየው የአድዋ ድል ዛሬ 125ኛ ዓመቱ በመላ ኢትዮጵያ በድምቀት ተከብሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም