ትውልዱ የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ክብር የማስጠበቅ ታሪካዊ አደራ አለበት - የአርበኞች ቤተሰቦች

61

አዲስ አበባ፣ የካቲት 23/2013 ( ኢዜአ) የአሁኑ ትውልድ የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ክብር የማስጠበቅ ታሪካዊ አደራ እንዳለበት ኢዜአ ያነጋገራቸው የአርበኞች ቤተሰቦች ገለጹ፤ በአድዋ ድል የተገኘውን አኩሪ ታሪክ ማክበር እንደሚገባውም አመልክተዋል።

125ኛው የአድዋ ድል በዓል ዛሬ በዳግማዊ ምኒሊክ አደባባይ በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የበዓሉ ታዳሚ የአርበኞች ቤተሰቦች የአድዋ ድል እኔ ልሙትልህና አንተ ቆይ በሚል ኢትዮጵያዊያን ለሕይወታቸው ሳይሳሱ ትልቅ ጀግንነት የፈጸሙበት መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያዊያን በጦርነቱ በአገር ፍቅር ስሜት ተነሳስተው በጋሻና በጎራዴ እየተዋጉ ታንክና መድፍ በመማረክ አስደናቂ ስራ መስራታቸውን አውስተዋል።

በአድዋ መሬቱ አርበኛ፤ ፈረሱ አርበኛ፤ ሕዝቡም አርበኛ በመሆን የተገኘው ድል ለኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም ነጻነትን ማጎናጸፉን ተናግረዋል።

አፄ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ ጦርነቱን በመምራትና ጠላትን ድል በማድረግ ያሳዩት ብልሃትና ጥበብ እጅጉን የሚደነቅ መሆኑን የገለጹት የአርበኞች ቤተሰቦች፤ በተለይም የአፄ ምኒልክ የጦርነት ክተት አዋጅ ኢትዮጵያን አንድ ያደረገና ለድሉ ቁልፍ ሚና የነበረው መሆኑን ጠቅሰዋል።

አባቶችና እናቶች ደምና አጥንታቸውን በመገበር ኢትዮጵያ ክብሯ እንዳይደፈር ማድረጋቸውንም ተናግረዋል።

የአሁኑ ትውልድም አባቶቹና እናቶቹ ያስረከቡትን አገር ሉዓላዊ ክብሯን የመጠበቅ ታሪካዊ አደራና ኃላፊነት እንዳለበት የአርበኞቹ ቤተሰቦች ገልጸዋል።

ትውልዱ የውስጥ ልዩነቶቹን ወደ ጎን በመተው በአድዋ የታየውን አንድነትና ሕብረት አሁን ኢትዮጵያ የገጠማትን ፈተናዎች ለመመከት ሊጠቀምበት እንደሚገባም ተናግረዋል።

የአድዋን ድል ታሪክ በሚገባ በማወቅና በመማር ድሉ ያስገኘውን ታሪክ ሊያከብረው እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት።

125ኛው የአድዋ ድል በዓል "አድዋ የሕብረ ብሔራዊ አንድነት አርማ" በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬ በመላው ኢትዮጵያ በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል።


የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም