“አድዋ ካስተማረን አንዱ ነገር ሕግን ማክበር ነው” – ዶክተር ሂሩት ካሣው

720

አዲስ አበባ፣ የካቲት 23/2013 (ኢዜአ )  አድዋ ካስተማረን አንዱ ነገር ሕግን ማክበር ነው ሲሉ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሣው ገለፁ።

125ኛውን የአድዋ ድል በዓል አስመልክቶ ትናንት ምሽት በብሔራዊ ቴአትር አዳራሽ የኪነ-ጥበብ ዝግጅት ተካሂዷል።


“አድዋ ካስተማረን አንዱ ሕግ ማክበር ነው” ያሉት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሣው ወራሪ ጠላት ‘እኔ ልግዛችሁ፤ እኔ ልወስንላችሁ’ ብሎ ሲመጣ አባቶቻችን ሕግ ነው ያስከበሩት ብለዋል።


ሰው ነጭ ጥቁር ተብሎ የተከፈለው በሚኖርበት አካባቢ ልዩነት ብቻ ነው ያሉት ሚኒስትሯ የሰው ልጅ ከተፃፈ ሕግ በፊት ሕገ-ልቦና እንደሚገዛው ገልፀዋል።

የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስትሯ ፊልሰን አብዱላሂ በበኩላቸው አድዋ አፍሪካዊያንን ጭምር ነፃ ያወጣ ድል መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም የአሁኑ ትውልድ ለነገው ትዉልድ ይህንን አደራ የማስረከብ ኃላፊነት አለበት ነው ያሉት።

የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በአድዋ ድል ነጮች ብቻ ሳይሆኑ የአፍሪካ አገራትም ይቀናሉ ብለዋል።

“ድሉ የነጮችን እብሪት ያበረደ የመጀመሪያ የጥቁር ሕዝቦች ድል ነው” ሲሉ ገልፀውታል።

“ኢትጵያዊያን አድዋን በፀሎታቸው ነው ያሸነፉት” ያለው ደግሞ የአሃዱ ራዲዮ ሥራ አስኪያጅ ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ ነው።

ጋዜጠኛ ጥበቡ አፍሪካዊያን የአድዋን ድል ምስጢር መርምረው በመጨረሻ የደረሱበት ድምዳሜ ድሉ በፀሎት ኃይል የመጣ መሆኑን ነው ሲል ገልጿል።

“ዝክረ አድዋ ኢትጵያዊነት” በተሰኘው የኪነ-ጥበብ ዝግጅት የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ቤተሰቦች፣ ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ሃላፊዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ታድመዋል።