የኮንትሮባንድና አደንዛዥ እፅ ዝውውርን ለመግታት ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተመለከተ

93

ሀዋሳ፣ የካቲት 23/2013 (ኢዜአ) በሀገሪቱ እየተስፋፋ የመጣውን የኮንትሮባንድና "ካናቢስ" አደንዛዥ እፅ ዝውውር ለመግታት ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተመለከተ።

በኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን የሀዋሳ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኮንትሮባንድና ህገ-ወጥ ንግድን መከላከልና መቆጣጠር በሚቻልበት ዙሪያ ከምዕራብ አርሲ ዞንና ወረዳዎች ከተወጣጡ ባለድርሻ አካላት ጋር በሻሸመኔ ከተማ የምክክር መድረክ ተካሄዷል።

በመድረኩ የጽህፈት ቤቱ የህግ ተገዥነት ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ኢዴሣ ለማ እንዳሉት፤ መስሪያ ቤቱ በየደረጃው ከተቋቋሙ የፀረ ኮንትሮባንድ እና ህገ- ወጥ ንግድ መከላከል ግብረ ሃይል ጋር በቅርበት እየሰራ ነው።

ሆኖም ከችግሩ ስፋት አንፃር ሲታይ የባለድርሻ አካላት ቅንጅትና ተሳትፎ አነስተኛ በመሆኑ የኮንትሮባንድ ፍሰቱ እየተስፋፋ መምጣቱን ተናግረዋል።

ባለፈው የበጀት ዓመት በወጪና ገቢ ኮንትሮባንድ ላይ በተደረገ ቁጥጥር 249 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው እቃዎች ሲያዙ በዘንድሮ በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ብቻ 301 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ መቆጣጠራቸውን አመላክተዋል።

ይህም የወጪና ገቢ የኮንትርባንድ ፍሰት በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መምጣቱን እንደሚያሳይ አቶ ኢዴሣ አስረድተዋል።

ኮንትሮባንድን በመከላከል በኩል ችግሮችን በየጊዜው እየገመገሙ በማስተካከል በኩል ያለው ሰፊ ክፍተት እንደተግዳሮት አንስተዋል።

በተለይ በምዕራብ አርሲ ዞን ወረዳዎች ውስጥ የሚመረተው ካናቢስ የተባለ አደንዛዥ እፅ በቀጥታ ወደ ውጭ እንደሚሄድ ተናግረዋል።

ይህም የሀገርን ገጽታ ከማበላሸት ባለፈ ለዜጎች ጤንነት ጠንቅ የሆነውን ምርት ከመከላከል ረገድ ችግሩን በሚመጥን መልኩ እንዳልተሰራ ገልጸዋል።

በሀገሪቱ ካናቢስ የማይሸጥና የማይለወጥ እንደሆነ የጠቆሙት አቶ ኢዴሣ በኬንያ ያለውን ዋጋ መሠረት በማድረግ ባለፉት ስድስት ወራት 100 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የካናቢስ ምርት ወደ ኬንያ ለማስወጣት ሲሞክር መቆጣጠራቸውን ጠቅሰዋል።

ህገ ወጥ ንግዱ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰትና ሀገሪቱ የምታገኘው የውጭ ምንዛሬ በከፍተኛ ሁኔታ ከመጉዳቱ ባለፈ በፀጥታና ሰላም ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ በመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ችግሩን ለመከላከል የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው አመልክተዋል።

የምክክር መድረኩ የተዘጋጀውም በቀጣይ ግብረ- ሃይሉ አሰራሮችንና ህጎችን በመፈተሽ፣ የኮንሮትባንድ መግቢያና መውጫ በሮችና መተላለፊያዎችን በመለየት የተጠናከረ ቁጥጥር ማድረግና ግንዛቤ ማስጨበጥ ላይ በትኩረት እንዲሰራ ሁኔታዎች ለማመቻቸት እንደሆነ አብራርተዋል።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የምዕራብ አርሲ ዞን ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ደረጀ ባይሣ በሰጡት አስተያየት ኮንትሮባንድንና ህገ ወጥ ንግድ መንግስት ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ በስርዓቱ ሰብስቦ ለልማት እንዳያውል ከፍተኛ ጫና እያሳደረ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

እንዲሁም የዜጎችን ጤንነት አደጋ ላይ እየጣለ በመሆኑ የዞኑ የፀጥታ መዋቅር ድርጊቱን ለመከላከል ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

በተለይ ከአደንዛዥ እፅ ጋር በተያያዘ በዞኑ ሻላ፣ ሻሸመኔና ከፊል አርሲ ነገሌ ወረዳዎች ውስጥ ችግሩ ጎልቶ እንደሚታይ ጠቅሰው ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅ ከግብርናና አስተዳደር አካላት ጋር በመሆን እጹን በሰብል ምርቶች ለመተካት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

የሻሸመኔ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀጂ መሀመድ በበኩላቸው በወረዳው ኮንትሮባንድና ህገ ወጥ ንግድን ለመግታት በተደረገ ጥረት የተገኘውን ውጤት የበለጠ ለማጎልበት የሁሉንም ባለድርሻ አካላት መናበብና ቅንጅት ያስፈልጋል ብለዋል።

በተለይ ከአደንዛዥ እፅ ጋር ተያይዞ ያሉትን ችግሮች በመረዳት ምርቱ ጥቅም ላይ እንዳይውል ለማጥፋት ከፀጥታ አካላት ጋር ሲሰራ መቆየቱን ጠቁመዋል።

አሁን ላይም አደንዛዥ እፅ የሚያመርቱና የሚያዘዋውሩ አካላትን ህብረተሰቡ አጋልጦ እንዲሰጥ ለማድረግ በቅርበት እየተሰራ መሆኑንም አመልከተዋል።

ለሁለት ቀናት በተካሄደው የምክክር መድረኩ ከጉምሩክ፣ከፌደራል ፖሊስና ከምዕራብ አርሲ ዞንና ወረዳዎች የተውጣጡ የአስተዳደር፣የፍትህ፣ የፀጥታ፣ የንግድና ገበያ ልማት አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም