"በስልጡን ምክክር ለነገ አዲስ ምዕራፍ" መድረክ የማጠቃለያ መርሃ ግብር እየተካሄደ ነው

69

አዲስ አበባ፣ የካቲት 23/2013 (ኢዜአ ) "በስልጡን ምክክር ለነገ አዲስ ምዕራፍ" በሚል ላለፉት ሶስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው መድረክ የማጠቃለያ መርሐ ግብር በወዳጅነት ፓርክ እየተካሄደ ነው።

የሠላም ሚኒስቴር ላለፉት ስድስት ወራት በመላ አገሪቷ የተለያዩ ክፍሎች ከመላ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ከ20 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በአገራዊ መግባባት ላይ ብሔራዊ የምክክር መድረኮች አካሂዷል። 

እነዚህን የምክክር መድረኮች ከአድዋ ድል ጋር በማስተሳሰር ከሁሉም የኅብረሰተብ ክፍሎች የተውጣጡ ተሳታፊዎችን ባካተተ አግባብ በአዲስ አበባ ወዳጅነት ፓርክ ለሦስት ቀናት ሲያካሂድ ቆይቷል። 

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴን፣ ሚኒስትሮችን፣ ጥሪ የተደረገላቸውን የውጭ አገራት ተወካዮችም ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በምክክር መድረኩ የማጠቃለያ መርሃ ግብር ታድመዋል።

የሠላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል በሰለጠነ ምክክር የነገ ተስፋ ምዕራፍ ማጠቃለያ መድረክ ንግግራቸው የአድዋ መንፈስ አሁንም ያለመሆኑን በብሔራዊ ምክክር መድረኮች ተገንዝበናል ብለዋል። 

እንደ መንግስት ኢትዮጵያዊ ሠላም እንዲፈጠር ተሳታፊዎች ያነሷቸውን የ'ቢሆኑ ሀሳቦች' ተቀብለናል ነው ያሉት ሚኒስትሯ።

መድረኩ በቅርፁ ከታች ወደላይ የሆነ፣ ነፃና ገለልተኛ በሆነ አግባብ ተሳታፊዎች አጀንዳ ቀርፀው የሚወያዩበት ኢትዮጵያዊ የሠላም ግንባታ መርሆዎች ላይ ያተኮረ እንደነበረ ገልፀዋል። 

በውይይቱም ኅብረተሰቡ ተሻጋሪ የሚሆኑ መፍትሔዎች ጠቋሚና የሠላም ባለቤት ራሱ መሆኑን አሳይቷል ነው ያሉት። 

ለሠላም፣ ይቅርታ፣ ዕርቅና አንድነት ያለው ያልተገደበ ፍላጎት የታየበት መሆኑንም ተናግረዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በማጠቃለያው 'በወዳጅነት ፓርክ ወዳጅነት መስርተዋል' ብለዋል። 

በአጠቃላይ ከምክክር መድረኩ የአድዋ መንፈስ አሁንም ያለ መሆኑን ያየንበት ነበር ብለዋል ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል።

ተሳታፊዎች በስልጡን ምክክሩ ያነሷውን ሀሳቦች መንግስት ሰምቷል፣ የሚታረሙትን እያረምን፣ ጠንካሮቹን እያጠናከርን እንቀጥላለን ነው ያሉት። 

ሚኒስትሯ ኢትዮጵያዊያን በጋራ ልባችንን አንድ አድርገን ኢትዮጵያን ከፍ ለማድረግ መስራት ይገባናል ሲሉም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም