የጉራጌ ህዝቦች ለመልማት በሚያደርጉት ጥረት ሁሉ የከተማ አስተዳደሩ ከጎናቸው ነው... ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ

110

የካቲት 23/2013(ኢዜአ) የጉራጌ ህዝቦች ለመልማት በሚያደርጉት ጥረት ሁሉ የከተማ አስተዳደሩ ከጎናቸው ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።

ምክትል ከንቲባዋ "አባቶቻችን እና እናቶቻችን በዓድዋ ያስመዘገቡትን ታሪካዊ ድል የእኛንም ትውልድ ታሪክ በልማት እንጽፋለን" በሚል የጉራጌ ልማት ማህበር ባዘጋጀዉ መርሃግብር ላይ ተገኝተዋል።

ወይዘሮ አዳነች በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ እንዳሰፈሩት "በመርሃ ግብሩ ላይ ከደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት አቶ ርስቱ ይርዳው ጋር ተገኝተን የጉራጌ ህዝቦች ለመልማት በሚያደርጉት ጥረት ሁሉ የከተማ አስተዳደሩ ከጎናቸው እንደሆነ ለመግለጽ እድል ስላገኘሁ ደስ ብሎኛል" ነው ያሉት።

"በግሌም እንዲህ ለልማት ከቆረጠ ማህበር ጋር በመሆን አዲስ አበባን በመተባበር እና በአብሮነት ለማልማት ቃል ገብቻለሁ" ብለዋል።

ሃገርን ማልማት ፣ ማበልጸግ እና መለወጥ መከባበርን፣ መድከምን፣ አብሮነትን እና ዝቅ ብሎ መስራትን እንደመጠየቁም የጉራጌ ህዝብም እነዚህ እሴቶችን ያዳበረ እና የስራ ወዳድነትን ጨምሮ ለሌሎች ማስተማር የሚችል ኢትዮጵያዊ በማለትም ገልጸዋል።

በሃገሪቱ እና በከተማዋ ዘላቂ ለውጥ ማምጣት የምንችለው ድህነትን በጋራ ተዋግተን በማሸነፍ ስንበለጽግ ፣ ብልጽግናችንም እያንዳንዳችንን ተጠቃሚ ሲያደርግ ነው ብለለዋል።

"የለውጡ አመራር አቋሙ ሁሉንም ማበረታታትና መላው ኢትዮጵያዊያንን አሳትፎና አደራጅቶ ለመምራት ስለሆነ ፣ሁላችሁም ለልማት ተደራጅታችሁ በሁሉም መንገድ ተሳተፉ፤ ከተማችንንም በጋራ በማበልጸግ አዲስ የድል ታሪክ እንጻፍ ለማለት እወዳለሁ" ሲሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም