ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትግራይ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች 216 ሺህ ብር አበረከቱ

100

የካቲት 23/2013(ኢዜአ)  ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ለትግራይ ክልል መልሶ ግንባታ ከመደመር መጽሃፍ ሽያጭ 200 ሺህ ብር እና የአንድ ወር ደመወዛቸውን ማበርከታቸውን የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ሙሉ ነጋ ገለጹ፡፡

ዋና ስራ አስፈጻሚው ይህን የገለጹት የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከተሞች አስተዳደሮች እና የሃረሪ ክልል ለትግራይ ክልል ያበረከቱትን ድጋፍ በተረከቡበት ጊዜ ነው፡፡

በክልሉ የደረሰው ችግር የትግራይ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያዊያን መሆኑን ዋና ስራ አስፈጻሚው ገልፀዋል፡፡

የትግራይ ሕዝብ በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደርና ለአገር አንድነት የታገለ ነው ያሉት ዶክተር ሙሉ በችግሩ ጊዜም ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ከጎኑ ሊቆሙ ይገባል ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድም ክልሉን መልሶ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት አሻራቸውን ማሳረፋቸውን ተናግረዋል፡፡

ከመደመር መጽሃፍ ሽያጭ ያገኙትን 200 ሺህ ብር፣ የአንድ ወር ደመወዛቸውንና ሶስት የውሃ ቦቴዎችን ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልፀዋል።

ዋና ስራ አስፈጻሚው አክለውም የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ከዓመት በጀቱ ላይ የ200 ሚሊዮን ብር ለክልሉ መልሶ ግንባታ ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባቱን ተናግረዋል፡፡

የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትም የ15 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማበርከቱን አውስተዋል፡፡

ለትግራይ ክልል ከጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ከሌሎች ክልሎች የተሰጡት ድጋፎች ትግራይን መልሶ በመገንባት ሂደት ውስጥ አቅም እንደሚሆኗቸውም ተናግረዋል፡፡

ዶክተር ሙሉ የተደረጉት ድጋፎች የትግራይ ሕዝብ በኢትዮጵያዊነቱ እንዲኮራ በችግሩ ወቅት የሚደርስለት ወገን እንዳለውም እንዲገነዘብ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

ለትግራይ ክልል መልሶ ግንባታ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተሞች አስተዳደሮች እና የሀረሪ ክልል በድምሩ ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸው ይታወቃል፡፡

በክልሉ በመንግስትና በግብረ ሰናይ ድርጅቶች እየተሰጠ ያለውን ሰብዓዊ ድጋፍ ለማገዝ የኦሮሚያ፣ የደቡብና የአፋር ክልሎችና የአዲስ አበባ አስተዳደር በርካታ የምግብ ቁሳቁሶች ድጋፍ ማድረጋቸው ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም