የደምበጫ-ሰቀላ እና ቢቡኝ ወረዳ የአስፋልት መንገድ ግንባታ ተጀመረ

319

የካቲት 23/2013 ( ኢዜአ) በአማራ ክልል የሚገኘው የደምበጫ-ሰቀላ እና ቢቡኝ ወረዳ የአስፋልት መንገድ ግንባታ ተጀመረ።

የደምበጫ-ሰቀላ እና የቢቡኝ ወረዳ አገናኝ 70 ኪ.ሜ የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት በመንግስት በሚሸፈን 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር የሚገነባ ነው።

በደጋ ዳሞት ፈረስ ቤት ከተማ ትናንት የፕሮጀከቱ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ሲከናወን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ አገኝሁ ተሻገር፣ የብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ብናልፍ አንዱዓለም እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የመንገዱ ግንባታ ሕዝቡ ለበርካታ ዓመታት ሲጠይቀው የነበረ መሆኑን ገልፀዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች በመንገድ እጦት እንግልትና ስቃይ ይደርሰበት እንደነበር ‘ምስክር መሆን እችላለሁ’ ያሉት አቶ ደመቀ ከ29 ዓመት በፊት በአካባቢው በመምህርነት ማገልገላቸውን አስታውሰዋል።

የመንገዱ ግንባታ የሕዝቡን ጥያቄ ከመመለስ ባሻገር ችግሮቹን ታሪክ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

የአማራ ክልል ፕሬዚዳት አቶ አገኝሁ ተሻገር በበኩላቸው በክልሉ ሕዝብ እየቀረቡ ያሉ በርካታ የልማት ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ እንደሚፈቱ ተናግረዋል።

በክልሉ መንገድን ጨምሮ ሌሎች የልማት ጥያቄዎችን በመለየት ፍትሃዊ የሆነ ምላሽ ለመስጠት እየተሰራ እንደሆነም ገልፀዋል።

“የሚገነቡት መንገዶች በሚፈለገው ጥራትና ፍጥነት እንዲጠናቀቁ የክልሉ መንግስት፣ ባለሃብቱ እንዲሁም  ኅብረተሰቡ ተቀናጅተን መስራት ይጠበቅብናል” ብለዋል አቶ አገኘሁ።

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝም በክልሉ የተጀመረው የመንገድ ግንባታ በጥራትና በፍጥነት ተጠናቆ ለተፈለገው ዓላማ እንዲውል ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል ይደረጋል ነው ያሉት።

መንገዱ አሁን ባለበት ሁኔታ በተሽከርካሪ 70 ኪሎ ሜትር ለመጓዝ ከ4 ሠዓት በላይ እንደሚወስድና ግንባታው ሲጠናቀቅ የሚፈጀው ጊዜ በግማሽ እንደሚያሳጥረው ገልፀዋል።

ከሠቀላ-አዴት የሚዘልቀውን 60 ኪሎ ሜትር የመንገድ ግንባታን በቀጣይ ወደ ስራ ለማስገባት በሂደት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

የአማራ መንገድ ስራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ አስማማው አለማየሁ ግንባታውን በተያዘለት ጊዜ አጠናቆ ለማስረከብ በትኩረት ይሠራል ብለዋል።

የደንበጫ-ሰቀላ እና ቢቡኝ ወረዳ መንገድ ግንባታ ለ1 ሺህ 500 የአካባቢው ነዋሪዎች የስራ ዕድል ይፈጥራል ተብሏል።