የአድዋ ድል ታሪክ በአግባቡ ተሰንዶ ለትውልድ ማስተማሪያነት ሊውል ይገባል-ጀግኖች አርበኞች ማህበር

645

ባህር ዳር፣ የካቲት 23/2013 (ኢዜአ) የጥንት አርበኞች ህብረትና አንድነት ያሳዩበት የአድዋ ድል ታሪክ በአግባቡ ተሰንዶ ለትውልድ ማስተማሪያነት ሊውል እንደሚገባ የአማራ ክልል የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር አስታወቀ።

የማህበሩ ሊቀመንበር አቶ ዳኝነት አያሌው ለኢዜአ እንዳሉት የአድዋ ድል መላ ኢትዮጵያዊያን በአልደፈርም ባይነት ከጫፍ እስከ ጫፍ በጠነከረ አንድነትን ያሳዩበት ታሪክ ነው።

የጥቁር ህዝቦች ምልክት የሆነው የአድዋ ድል በዓል ላለፉት ሶስት አስርት ዓመታት በአግባቡ ባለመከበሩ ታሪኩ በተተኪው ትውልድ ዘንድ በአግባቡ እንዳይታወቅ ጫና ፈጥሮ መቆየቱን አስታውሰዋል ።

“ታሪኩ በአግባቡ እንዲታወቅ ባለመደረጉ ትውልዱ ከአባቶቹና አያቶቹ የወረሰውን ለሀገር አንድነትና ፍቅር መስዋትነት መክፈልን በቅጡ እንዳያውቅ አድርጎታል” ብለዋል።

“የኢትዮጵያዊነት የነፃነት ማሳያ የሆነው የአድዋ ድል ከትውልድ ትውልድ እንዲተላለፍና ለሃገር ግንባታ እንዲውል ታሪኩ በትክክል ተሰንዶ ጥቅም ላይ ሊውል ይገባል” ሲሉ አመልክተዋል።

የአድዋ ድል መነሻ የሆኑ ታሪካዊ ቦታዎችን የቱሪዝም መዳረሻ በማድረግ ታሪኩ በአግባቡ እንዲታወቅ ማድረግ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ የትምህርት ተቋማት የኢትዮጵያን አኩሪና ገናና ታሪክ የሆነውን የአድዋ ድል  ትክክለኛውን ታሪክ  ለትውልድ ማስተማርና ማሳወቅ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

አድዋን ስናስብ ቅኝ ገዥ፣ ወራሪና ባንዳን በሌላ በኩል ደግሞ የነፃነት አርበኞችን የትግል ታሪክ እናስታውሳለን ያሉት ደግሞ የማህበሩ ዋና ፀሐፊ አቶ ጌጡ ደሴ ናቸው።

”ዓለም እንደሚያውቀው የአድዋ ድል በአርበኞቻችን የከበረ መስዋዕትነት የተገኘ የአንድነትና የጀግንነት ማህተም የታተመበት መለዮአችን ነው” ሲሉ ገልፀዋል።

“የአድዋ ድል አሁን ላይ በሃገራችን የተዘራውን በቋንቋ፣ በዘር፣ በሃይማኖት፣ በጎሳ የመከፋፈል ፈተና ማጥፊያ ሆኖ ለትውልዱ ጥቅም ላይ ሊውል ግድ ነው” ብለዋል።

125ኛው አመት የአድዋ ድል መታሰቢያ በዓል ዛሬ በሀገር አቀፍ ደረጃ በድምቀት እየተከበረ ይገኛል።