የቡድን 20 አባል አገራት የዕዳ ማቃለያ ማዕቀፍ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ የዕዳ እፎይታ ይሰጣታል

71

አዲስ አበባ፣ የካቲት 22/2013 ዓም (ኢዜአ )የቡድን 20 አባል አገራት የዕዳ ማቃለያ ማዕቀፍ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ የዕዳ እፎይታ እንደሚሰጣት የገንዘብ ሚኒስቴር ገለፀ።

ባለፈው አንድ ዓመት ከስድስት ወር አጠቃላይ የኢትዮጵያ የብድር ጫና ከ6 እስከ 7 በመቶ መቀነሱንም አመልክቷል።

በሳዑዲ ዓረቢያ አስተናጋጅነት በ2012 ዓ.ም በተካሄደው የቡድን 20 አባል አገራት ስብሰባ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የተጎዳውን የዓለም ኢኮኖሚ ለመደገፍ ለታዳጊ አገራት የብድር እፎይታ ጊዜ መስጠታቸው የሚታወስ ነው።

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ በቡድን 20 አባል አገራት የእፎይታ ተጠቃሚ ከሆኑት አገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ እንደነበረች አስታውሰዋል።

የተሰጠው የብድር እፎይታ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ባስከተለው የኢኮኖሚ ተጽእኖ ታዳጊ አገራት ጫና ውስጥ እንዳይገቡና ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያከናውኑትን ስራ ለማገዝ መሆኑን ገልጸዋል።

ይሁንና የእፎይታ ጊዜ አጭር መሆኑን ከግምት በማስገባት የቡድን 20 አባል አገራት ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ጋር በመሆን የዕዳ ማቅለያ ማዕቀፍ ማዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

የዕዳ ማቅለያ ማዕቀፉ ለወራት የነበረው የብድር እፎይታ ጊዜ ለዓመታት እንዲሆን የሚያደርግ መሆኑንና በማዕቀፉ ተጠቃሚ መሆን የሚፈልጉ አገራት ሊያሟሏቸው የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎችን መያዙን አመልክተዋል።

ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት /አይ.ኤም.ኤፍ/ ጋር በኢኮኖሚ ማሻሻያ ስራዎች ላይ በትብብር መስራትና ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ተግባራዊ ማድረግ ዋነኛ መስፈርቶች መሆናቸውን አብራርተዋል።

ኢትዮጵያም በቡድን 20 አባል አገራት የቀረበውን መስፈርት ከሚያሟሉ ጥቂት አገራት መካከል አንዷ መሆኗንና የዕዳ ማቅለያ ማዕቀፉን በደስታ እንደምትቀበለው ገልጸዋል።

የቡድን 20 አባል አገራት የዕዳ ማቃለያ ማዕቀፍ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ የብድር እፎይታ የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በማዕቀፉ አማካኝነት የብድር መክፊያ ጊዜዋን ማሸጋሸግ እንትምትችልና ይህም በየዓመቱ ለዕዳ ክፍያ የምታወጣውን 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ለሌሎች የልማት ስራዎች ፈሰስ ለማድረግ እንደሚያግዛት ገልፀዋል።

መንግስት ኢትዮጵያ በዕዳ ማቅለያ ማዕቀፉ ተጠቃሚ እንድትሆን የሚያስችሏትን ስራዎች ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ጋር በመተባበር እያከናወነ እንደሚገኝ ነው ሚኒስትር ዴኤታው ያስረዱት።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ መንግስት በአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው የዕዳ ጫናን ለማቃለል በወሰዳቸው እርምጃዎች ባለፈው አንድ ዓመት ከስድስት ወር አጠቃላይ የኢትዮጵያ የዕዳ ጫና ከስድስት እስከ ሰባት በመቶ መቀነሱን ገልጸዋል።

ይህም የዕዳ ጫናው ከአጠቃላይ አገራዊ ምርት መጠን ጋር ሲነጻጻር የነበረው ድርሻ ወደ 51 ነጥብ 5 በመቶ ዝቅ ማለቱን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ አጠቃላይ የዕዳ ጫና ስጋት ከከፍተኛ ወደ መካከለኛ ደረጃ መሸጋገሩን በመጠቆም።

በሌላ በኩል ዓለም አቀፍ የፋይናንናስ ተቋማት የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ዕድገት አስመልክተው የሚያወጧቸው ትንበያዎች በአብዛኛው የተሳሳቱ መሆናቸውን ነው ዶክተር እዮብ የገለጹት።

የሚደረጉት ትንበያዎች የኢትዮጵያ መሰረታዊ የኢኮኖሚ ሁኔታና የዕድገት ምንጮችን ያላገናዘቡ በመሆናቸው መንግስት ይህን የማስረዳት ተግባር እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።

የኢኮኖሚ ሁኔታውን በማስረዳት እየተከናወነ ባለው ስራ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ያላቸውን እይታ እየቀየሩ መምጣታቸውንና በትንበያዎቻቸው የሚጠቀሟቸው ማመላከቻዎች እየተሻሻሉ መሆኑን ገልጸዋል።

መንግስት በአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ጨምሮ ሌሎች የማክሮ ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ችግሮችን ለመፍታት እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

በሌላ በኩል በቴሌኮም ዘርፍፉ ለሚሰማሩ ሁለት ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ፈቃድ ለመስጠት የተጀመረው ሂደት በተያዘለት ጊዜ እየተከናወነ መሆኑን ነው ሚኒስትር ዴኤታው የገለጹት።

ባለፈው ሳምንት መንግስት ፈቃድ ለመስጠት ባወጣው ጨረታ ዙሪያና በሂደቱ ጉዳዮች ከተጫራቾች ጋር ውይይት መደረጉን ጠቅሰዋል።

ተጫራቾች ያነሷቸውን ሀሳቦች መሰረት በማድረግ መንግስት ማሻሻያ ያደረገበትን የጨረታ ሰነድ በዚህ ሳምንት ለተወዳዳሪዎች ይልካል።

ተወዳዳሪዎችም እስከ መጋቢት 27 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ የጨረታ ሰነዳቸውን እንዲያስገቡ የጊዜ ገደብ ተቀምጧል።

ኢትዮ-ቴሌኮምን በከፊል ወደ ግሉ ዘርፍ ለማዞር የተጀመረው ስራ የቴሌኮም ፈቃድ ከመስጠት ጎን ለጎን እየተከናወነ ነው ብለዋል።

ድርጅቱን ወደ ግሉ ዘርፍ ማዞር ላይ የሚሰራው ቡድን የመጨረሻውን የቢዝነስና ግምገማ ሰነድ እያዘጋጀ መሆኑንና ሰነዱ ተዘጋጅቶ ሲጠናቀቅ ተጫራጮችን እንደሚጋብዝ ተናግረዋል።

የቴሌኮም ፈቃድ የመስጠቱ ሂደት ኢትዮጵያን ተጠቃሚ በሚያደርግና ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ግልጽነትና ፍትሃዊነት በተሞላበት መልኩ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

ዶክተር እዮብ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚውን ዘርፍ ለግሉ ዘርፍ ክፍት የማድረጉ ስራ በከፍተኛ ጥንቃቄና በተጠና መንገድ እየተከናወነ እንደሚገኝ አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም