የአድዋ ድል የኢትዮጵያውያን የአንድነት ውጤት መሆኑ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የአድዋ ድል የኢትዮጵያውያን የአንድነት ውጤት መሆኑ ተገለጸ

ሶዶ፤ የካቲት 22/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያውያን የጣሊያን ወራሪ ሀይል ላይ ያስመዘገቡት የአድዋ ድል የመላው ህዝብ የጋራ ውጤት መሆኑ ተገለጸ።
125ኛው የአድዋ ድል በዓል በደበብ ክልል ደረጃ በወላይታ ሶዶ ከተማ በተለያዩ መርሃ ግብሮች ተከብሯል።
በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የደቡብ ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ሃላፊ አቶ ሃይለማሪያም ተስፋዬ እንዳሉት የአድዋ ድል ከሁሉም አቅጣጫ የዘመቱ ኢትዮጵያውያን አንድነት ውጤት ነው።
“ድሉ የኢትዮጵያውያን ህብረ ብሄራዊነት ማህተም ነው፤ ጀግኖች አርበኞች በሀገር ጉዳይ ወደኋላ እንደማይሉ ቆራጥና አይበገሬ መሆናቸውን ያሳዩበት ነው” ብለዋል።
በአድዋ ጀግኖች አባቶች ወራሪውን ሊያሸንፉ የቻሉት ልዩነትን ወደጎን በመተው በፈጠሩት ጠንካራ አንድነት ነው ያሉት አቶ ሃይለማሪያም ይህን ፈለግ በመከተል በልማቱ ጠንክረን መስራት ይገባናል ሲሉም ተናግረዋል።
የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር እንድሪያስ ጌታ በበኩላቸው የጀግኖች አባቶች አኩሪ ገድል ለዘላለም ሲዘከር የሚኖር ታሪክ መሆኑን ገልጸዋል።
ለአንድ ዓላማ ከተሰለፍን የትኛውንም ተገዳዳሪ ሃይል ማሸነፍ እንደሚቻል ወጣቱ ትውልድ ሊማርበት ይገባል ብለዋል።
የወላይታ ህዝብ ከሌሎች ከኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን የሃገርን ዳር ድንበር ለማስከበር ከፍተኛ መስዋዕትነት መክፈሉንም አስታውሰው የተጀመሩ የልማት ዕቅዶች ከግብ ለማድረስ ህዝቡ የሚያደርገውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንዲቀጥልም መልዕክታቸቸውን አስተላልፈዋል።
የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር የደቡብ ክልል ሊቀመንበር አቶ የኋላሸት ቸርነት በዓሉን በዚህ መልኩ በድምቀት ማክበር ከታሪክ ሊቀሰም የሚገባውን ዕውቀት ለማስጨበጥ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል፡፡
ሃገር የቆመችው አባቶች በከፈሉት የህይወት መስዋዕትነት መሆኑን በመረዳት ወጣቱ አንድነታችንን ለመሸርሸር የሚደረገውን ሙከራ ለማክሸፍ መንቃት አለበት ብለዋል፡፡
የአድዋ ድል በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ የማሸነፍ ወኔ ስንቅ ነው ያሉት ደግሞ በኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ሶስተኛ አየር ወለድ ብርጌድ የሁለተኛ ሻለቃ ምክትል አዛዥ ሻለቃ አሸናፊ ጥላሁን ናቸው።
ድሉ ኢትዮጵያዊያን የሃገርን ሉዓላዊነት ለመፈታተን የሚቃጣ ሃይልን ለመመከት እንደሚቻል ያሳየ መሆኑንም ገልጸዋል።
በበዓሉ የአድዋ ድል ለአብሮነትና ሃገራዊ አንድነት ባለው ፋይዳ ዙሪያ ጥናታዊ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡