የዓድዋ ድል እውነተኛ ታሪክ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ ከምሁራን ብዙ ይጠበቃል... ሚኒስትር ዶክተር ሒሩት ካሳው

129

የካቲት 22/2013(ኢዜአ) የአድዋ ድል እውነተኛ ታሪክ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ ከምሁራን ብዙ እንደሚጠበቅ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሒሩት ካሳው ተናገሩ።

ባለፉት ዓመታት የተዛባውን ታሪክ ለማስተካከል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ብዙ መስራት እንዳለባቸውም አመልክተዋል።

125ኛውን የዓድዋ ድል በዓል በማስመልከት "ዓድዋ በታሪክ ምሁራን ዕይታ" በሚል መሪ ሃሳብ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የተዘጋጀ የውይይት መድረክ ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

ሚኒስትሯ በዚሁ ጊዜ ባደረጉት ንግግር የአድዋ ድል እውነተኛ ታሪክ ተጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ ከምሁራን ብዙ መስራት ይጠበቃል።

ምሁራን በአድዋ ድል ላይ የተለያዩ ጥናቶችን አካሂደው ለታሪክ እንዲቀመጡ በማድረግ ከነበረው በተጨማሪ መስራት ይኖርባቸዋልም ብለዋል።

የአድዋ ድል ታሪክ ከኢትዮጵያ አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ አሁን ካለበት የበለጠ እንዲታወቅ ምሁራን ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው አመልክተዋል።

ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው ፍቅር በአንድነት ወራሪውን የጣሊያን ጦር ድል ያደረጉበት 125ኛ ዓመት የአድዋ ድል በዓል ለአንድ ወር በመላ አገሪቷ በተለያዩ ዝግጅቶች ሲከበር መቆየቱን አስታውሰዋል።

ሚኒስትሯ "በቀጣይ የአድዋ ድል በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ እንዲካተት ይሰራል፤ መገናኛ ብዙሃንም ስለ አድዋ ድል የበለጠ መናገር አለባቸው" ብለዋል።

ባለፉት 30 ዓመታት የኢትዮጵያ ታሪክ አቀራረብ ሆን ተብሎ እንዲዛባ መደረጉን ያወሱት ሚኒስትሯ፤ ይህን ለማስተካከል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ብዙ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

"አድዋ እና ኢትዮጵያዊነት-የአድዋ ድል ኢትዮጵያዊነትና ሕብረ ብሔራዊነትን ከማጠናከር አኳያ ያለው አንድምታ" በሚል የመወያያ ጽሁፍ ያቀረቡት ዶክተር አልማው ክፍሌ ዛሬም በአንድነት፣ በመተባበርና በመደማመጥ አገርን ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።

"የኢትዮጵያን አንድነት ለዘመናት ለማስቀጠልና ለማቆየት የአድዋን ድል በአርአያነት መጠቀም አለብን" ነው ያሉት።

በጦርነቱ ኢትዮጵያዊያን ያሳዩት ኅብረት ጠላትን አሳፍሮ እንደመለሰ ሁሉ አሁንም በአንድነት ለአገር ልማት መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ሌላው የመወያያ ጽሁፍ አቅራቢ ዶክተር አየለ በከሬ "የአሁኑ ማንነታችን በአድዋ ድል የተገነባ በመሆኑ የአባቶቻችንን ድል ጠብቀን ለትውልድ ማስተላለፍ አለብን" ብለዋል።

የጣሊያን ወራሪ ኃይል በወቅቱ ኢትዮጵያዊያንን ለመከፋፈል ቢሞክርም ሕዝቡ በአንድነቱ ጠላትን ድል ሊያደርግ መቻሉንና ከዛ መማር እንደሚገባ ጠቁመዋል።

"በወቅቱ የኢትዮጵያ ንጉስ የነበሩት አጼ ምኒልክ የተሳካ የአመራር ጥበብ መጠቀማቸው የጠላት ጦር ድል እንዲሆን አድርጓል" ያሉት ደግሞ "አቅም ገንቢና አቅም አዋቂ ምኒልክ" በሚል በመድረኩ የመወያያ ጽሁፍ ያቀረቡት ፕሮፌሰር ሹመት ሲሻኝ ናቸው።

ከሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢ የመጡ አርበኞችን በአንድነት አስተባብረው በጦርነቱ እንዲሳተፉ በማድረጋቸው ድል ማስመዝገብ ተችሏል ብለዋል።

"እቴጌ ጣይቱ በበኩላቸው ጦሩን በማስተባበርና በመምራት እንዲሁም ንጉሱን በማማከር ድሉ እንዲሳካ አድርገዋል" ሲሉ አክለዋል።

በአገር ፍቅርና በተደፈርኩ ስሜት የኢትዮጵያ አርሶ አደር ሠራዊት ከአንድ ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ በእግሩ ተጉዞ በጠላት ላይ ድል መቀዳጀቱንም ተናግረዋል።

የአድዋ ድል አውሮፓዊያን የኢትዮጵያን ነጻት በግድ እንዲቀበሉ ያደረገ እንደነበረም ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም