ገበያውን ለማረጋጋት ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ምርቶችን ለመንግስት የልማት ድርጅቶች አቅርበው እንዲከፋፈል ሊደረግ ነው

85

አዲስ አበባ፣ የካቲት 22/2013 ( ኢዜአ)  መንግስት ገበያውን ለማረጋጋት ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ምርቶችን ለመንግስት የልማት ድርጅቶች አቅርበው እንዲከፋፈል ሊደረግ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ለዳቦ ፋብሪካዎች በገበያ ዋጋ የሚከፋፈል ስንዴ ወደ አገር ውስጥ መግባቱንም ገልጿል።

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ስራዎችና ወቅታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

መንግስት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ለመጣው የኑሮ ውድነት በአጠቃላይ ለዋጋ ንረት መፍትሔ ለመስጠት በአጭርና በረጅም ጊዜ የሚወስዳቸው እርምጃዎች ምንድናቸው? የሚል ጥያቄ ከጋዜጠኞች ቀርቦላቸዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው መንግስት አሁን ያለውን የዋጋ ንረትና ገበያውን ለማረጋጋት የሚያስችል የአጭር ጊዜ መፍትሔዎችን ተግባራዊ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

መንግስት ገበያውን ለማረጋጋት በቀጥታ ግዥ ምርቶችን ከዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በመግዛት ለመንግስት የልማት ድርጅቶች በማቅረብ የሚከፋፈልበት አሰራር ተግባራዊ እንደሚሆን ተናግረዋል።

ምርቶቹን በ'አለ በጅምላ'ና በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት መጋዘኖች በማስገባት የማከፋፈል ስራ እንደሚከናወንና ከከዚህ በፊቱ በተለየ መልኩ መንግስት ጣልቃ በመግባት በክፍፍሉ ላይ ክትትልና ቁጥጥር እንደሚያደርግ ገልፀዋል።

በመንግስት የልማት ድርጅቶች በኩል ምርቶቹን የማከፋፈል ስራው በአጭር ጊዜ ተግባራዊ እንደሚደረግና ገበያው ላይም መረጋጋት ከመፍጠር አኳያ የራሱን ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል።

የነዳጅ ጭማሪውን ተከትሎ ከጭማሪው ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የሌላቸው ምርቶች ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ አካላት ላይ አስተዳደራዊና ሕጋዊ እርምጃ ይወሰዳልም ብለዋል።

መንግስት አሁን የታየው የዋጋ ንረት ዋነኛ ምክንያት የንግድ አሻጥር ነው ብሎ እንደማያምንና የችግሩ መንስኤ የንግድ ስርዓቱ ችግር መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ጠቁመዋል።

አንድ አርሶ አደር በ10 ብር ለገበያ ያቀረበውን አቮካዶ በ40 ብር መሸጥ የንግድ አሻጥር ሳይሆን የንግድ ስርዓቱ ችግር ማሳያ መሆኑን አብነት ጠቅሰዋል።

መንግስት ለችግሩ መንስኤ እኔ አይደለሁም ከማለት ይልቅ የንግድ ስርዓቱን ችግር መፍታት ላይ በትኩረት መስራት አለበት የሚለው ሀሳብ ተገቢ መሆኑንም ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የዳቦ አምራቾች የገጠማቸውን የስንዴ እጥረት ለመፍታት መንግስት በግዥ ያመጣው ስንዴ ወደ አገር ውስጥ መግባቱንና የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በቅርቡ ለአምራቾች በገበያ ዋጋ እንደሚያከፋፍል ነው ዶክተር ኢዮብ ያስረዱት።

አሁን ያለው የዋጋ ንረት ባለፉት ከ10 እስከ 15 ዓመታት ጊዜ የተከማቸ የዋጋ ንረት ውጤት ነው ብለዋል።

ከዋጋ ንረቱ 60 በመቶውን የሚይዘው የምግብ ምርቶች ዋጋ እንደሆነ፤ ለዚህም ምርታማነትን ማሳደግና የንግድ ስርዓቱን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት መንግስት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም የግብርናውን ዘርፍ ሜካናይዝድ በማድረግ ምርታማነትን ለማሳደግ አርሶ አደሩን በሰፋፊ የእርሻ ልማት ኢንቨስትመንት ስራዎች ለማሳተፍ እየተከናወነ ያለው ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የዋጋ ንረት በአጠቃላይ የኑሮ ውድነት መፍትሔ የሚያገኙት በአጭር ጊዜ በሚወሰዱ እርምጃዎች እንዳልሆነም ተናግረዋል።

መንግስት በአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብሩ ትኩረት ከሰጣቸው ዋነኛ ጉዳዮች አንዱ ለዋጋ ንረትና ለኑሮ ውድነት መንስኤ የሆኑ መዋቅራዊ ችግሮችን መፍታት እንደሆነም አመልክተዋል።

በመርሃ ግብሩ አማካኝነት የሚከናወኑ ስራዎች አሁን የማይታዩ ነገር ግን በረጅም ጊዜ ለውጥ የሚያመጡ መፍትሔዎችን እንደሚያስገኝ ነው ሚኒስትር ዴኤታው ያብራሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም