ወጣቶች አንድነትን፣ መተባበርንና አብሮነትን ከአድዋ ድል ሊማሩ ይገባል

94

አዲስ አበባ፣ የካቲት 22/2013 ( ኢዜአ) ወጣቶች አንድነትና መተባበርን ከአድዋ ድል ሊማሩ እንደሚገባ "በስልጡን ምክክር አዲስ የተስፋ ምዕራፍ" የተሰኘው ብሔራዊ የውይይት መድረክ ታዳሚዎች ገለጹ።

ሠላም ሚኒስቴርና ዴስቲኒ ኢትዮጵያ በጋራ ያዘጋጁት "በስልጡን ምክክር አዲስ የተስፋ ምዕራፍ" የተሰኘው ብሔራዊ የውይይት መድረክ ሦስተኛ ቀኑን ይዟል።

በውይይት መድረኩ ከመላው ኢትዮጵያ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የወከሉ ከ1 ሺህ 200 በላይ ሰዎች እየተሳተፉ ነው።

ተሳታፊዎቹ በአገር አንድነትና በብሔራዊ መግባባት ላይ ያተኮሩ ውይይቶችን በማካሄድ ላይ ይገኛሉ።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የውይይቱ ተሳታፊዎች ወጣቶች አንድነትን፣ መተባበርንና አብሮነትን ከአድዋ ድል ሊማሩ እንደሚገባ ነው የገለጹት።

ወጣት ሚካኤል ያቦነህ ውይይቱ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ያካተተ መሆኑ የተለየ ስሜት እንደፈጠረበት ተናግሯል።

አድዋ ላይ ከአራቱ የአገሪቱ አቅጣጫዎች የመጡ ጀግኖች አባቶችና እናቶች አንድ ሆነው በመተባበር ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቀውን የኢጣሊያ ወራሪ ኃይል ማሸነፍ ችለዋል፤ አሁን ጦርነት ውስጥ ያለነው ድህነት፣ አለመግባባትና ዘረኝነትን ለማሸነፍ ነው ሲል ነው የገለጸው።

ወጣቶች ከአድዋ ድል ተምረው ኅብረትና አንድነታቸውን በማጠንከር ይህን ጦርነት ድል መንሳት እንዳለባቸውም ተናግሯል።

የአድዋ ድል በዓል መከበር የአሁኑን ትውልድ በይበልጥም ወጣቱን ለተጨማሪ ድሎች እንደሚያነሳሳ ነው ወጣቱ የገለጸው።

ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ ወጣት አንዱአለም እንዳሻው በበኩሉ በአገር ጉዳይ ላይ ለመወያየት ከመላው ኢትዮጵያ የተወከሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች መሳተፋቸው ከአድዋ ድል ጋር እንደሚያመሳስለው ተናግሯል።

"አባቶቻችን አንድ በመሆናቸው በባዶ እግራቸው ተዋግተው ጣልያንን ድል አድርገዋል" ያለው ወጣቱ፤ ድሉ ለዛሬው ወጣት ከምንም በላይ አገርን ማስቀደምንና በመተባበር ውጤት ማምጣት እንደሚቻል የሚያስተምር መሆኑን ገልጿል።

"የአድዋ ድል ከኢትዮጵያ አልፎ ለመላው ጥቁር ሕዝቦች ነጻነት ያመጣ ነው" ያሉት ደግሞ አባት አርበኛ ዋና ሳጂን ባሻ ስዩም ኪዳኑ ናቸው።

የአድዋ ድል እንዲሁ ዝም ብሎ የተገኘ ሳይሆን አርበኞች ደምና አጥንታቸውን ገብረው ያመጡት ታላቅ ድል ነው ብለዋል።

የአድዋ ድል ኢትዮጵያ የመላውን ጥቁር ሕዝብ ነጻነት ለዓለም ያበሰረችበት ነው ሲሉም አክለዋል።

ወጣቶች እርስ በእርስ መገፋፋትን ትተው ለጋራ ዓላማ በአንድነት በመቆም አገራቸውን ሊያሳድጉ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም