የአገር ሽማግሌዎች የወረዳውን ሰላም በዘላቂነት ለማስቀጠል በዞኑ ከተቋቋመው የተቀናጀ ግብረ ሃይል ጋር እንደሚሰሩ ገለፁ

303

የካቲት 22/2013 ( ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የፓዊ ወረዳ የአገር ሽማግሌዎችና አመራሮች የወረዳውን ሰላም በዘላቂነት ለማስቀጠል በዞኑ ከቋቋመው የተቀናጀ ግብረ ሃይል ጋር እንደሚሰሩ ገለጹ።

በመተከል ዞን የተቋቋመው የተቀናጀ ግብረ ሃይል አስተባባሪ እና የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የጸጥታ ቢሮ እንዲሁም የዞኑ አስተዳዳር ከፓዌ ወረዳ ከተወጣጡ የአገር ሽማግሌዎችና አመራሮች ጋር በወረዳው ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል።

ከውይይቱ በኋላ በወረዳው እየተካሄደ ያለውን የመስኖ ልማት ፕሮጀክት ጎብኝተዋል።

የአገር ሽማግሌዎቹ በዞኑ የተቋቋመው ግብረ ሃይል በአጭር ጊዜ ውስጥ በአካባቢው ሰላም እንዲረጋገጥና ማህበረሰቡ ወደነበረበት እንቅስቃሴ እንዲመለስ እየተሰራ ስላለው ተግባር አመስግነዋል።

በዞኑ ሰላም እንዳይሰፍን ያደረጉ የጥፋት ሃይሎችን በቅንጅትና በትብብር በመታገል በአካባቢው ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍንና አንድም ዜጋ እንዳይሞት የማድረግ ግዴታ አለብን ብለዋል።

የወረዳው አመራሮችም ግብረ ሃይሉ የህይወት መስዋትነት በመክፈል ጭምር በአጭር ጊዜ ችግሩን በማስወገድ የህዝቡ ሰላም እንዲመለስ እየሰራ ባለው ስራ ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

አመራሮቹ ግብረ ሃይሉ ያቀዳቸው ዕቅዶች ከግብ እንዲደርሱ በቅንጅት ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል። 

የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል የፀጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ አብዮት አልቦሮ አመራሩ የህዝቡን ችግር ለመቅረፍ መስራት አለበት ብለዋል።

አመራሩ በቅንነትና በታማኝነት ህዝቡን ማገልገል እንዳለበትም አቶ አብዮት አመልክተዋል።

በመተከል ዞን የተቀናጀ ግብረ ሃይል ዋና አስተባባሪ ሌተናል ጄኔራል አስራት ዴኔሮ ግብረ ሃይሉ በሁለት ወራት ውስጥ የዞኑን ፀጥታና ሰላም ከማስፈን በተጨማሪ ህዝብን መልሶ የማደራጀት ተግባራትን አከናውኗል ብለዋል፡፡

በተጨማሪ አንድነት ከማረጋገጥ እና የተቋረጡ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች እንዲጀመሩ ከማድረግ አኳያ የተሰሩ ስራዎች ያመጡትን ለውጥ ለመፈተሽ እና በቀጣይ የህዝቡ ሚና ምን መሆን እንዳለበት በሚል ውይይት መደረጉን ተናግረዋል።

በዚህም ወቅት የፓዌ ወረዳን ጨምሮ በዞኑ ያሉ ሁሉም ወረዳዎች ወደ ነበሩበት ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲመለሱ ፣ የተዘጉ መንገዶች፣ ትምህርት ቤቶች እና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ስራ መጀመራቸውን አስታውቀዋል ።

ጄኔራል አስራት የፀጥታ ስራ ሁለገብ እና በቅንጅት የሚሰራ እንደሆነ ገልጸው የአገር ሽማግሌዎችና አመራሮች በዞኑ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን በትኩረት መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

አመራሩ ከቡድን አስተሳሰብ በመውጣት ህዝብን በእኩልነት ለማገልገል እና ችግሮችን በውይይት እና በመነጋገር መፍታት አለበት ብለዋል።

አመራሮቹ ከውይይቱ በኋላ በወረዳው እየተሰራ ያለውን የመስኖ ልማት ፕሮጀክት የጎበኙ ሲሆን የአካባቢው ነዋሪዎች ሰላምን ከማስጠበቅ ጎን ጎን የልማት ስራዎችን ማስቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በመተከል ዞን የተቋቋመው የተቀናጀ ግብረ ሃይል በህዝቦች መካከል አንድነት፣ ሰላም እና ልማት እንዲመጣ እየሰራ ይገኛል።