በባሌ ዞን የቡና ልማትን ለማስፋፋት ከ15 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ተዘጋጀ

71

ጎባ፤ የካቲት 22/2013 (ኢዜአ) በባሌ ዞን የቡና ልማትን ለማስፋፋት ከ15 ሚሊዮን በላይ የተሻሻሉ የቡና ችግኞች ለተከላ መዘጋጀታቸውን የዞኑ የእርሻና ተፈጥሮ ኃብት ልማት ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡

የቡና ችግኞቹ ከጅማና መቻራ የግብርና ምርምር ማዕከላት የተገኙና በሄክታር እስከ 12 ኩንታል ምርት እንደሚሰጡ በምርምር የተረጋገጡ ጨምሮ  15 ዓይነት ዝርያዎች ሲሆኑ በሽታን በመቋቋም የተሻለ ምርት የሚሰጡ መሆናቸው ተመልክቷል።

በጽህፈት ቤቱ የቡና ልማት፣ ጥራትና ቅመማ ቅመም ቡድን መሪ አቶ ወንዶሰን ነጋ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ለመጪው የክረምት ወቅት ለተከላ የተዘጋጁት የቡና ችግኞቹ  በዞኑ አምስት ቡና አብቃይ ወረዳዎች ውስጥ ነው፡፡

ምርጥ የቡና ችግኞቹ  በ653 የመንግስትና ግል የቡና ችግኝ ጣቢያዎች እንደተዘጋጁ የጠቆሙት የቡድን መሪው ችግኞቹ ከ6ሺህ ሄክታር መሬት ለመሸፈን ያስችላሉም ብለዋል፡፡

በቡና ልማትና በችግኝ የተከላ ሂደቱ ላይ ከ24 ሺህ በላይ አርሶና አርብቶ አደሮች በመሳተፍ ላይ ናቸው ።

በዞኑ የቡና ልማት በየዓመቱ እየተስፋፋ መሆኑን አመልክተው አምና ከተተከለው አስራ ሶስት ሚሊዮን የቡና ችግኝ ውስጥ 85 በመቶ መጽደቁንም አስታውሰዋል፡፡

በቡና ልማቱ እየተሳተፉ ካሉት መካከል የሀረና ቡሉቅ ወረዳ አርሶ አደር  ሃጂ ኡመር ባቲ በሰጡት አስተያየት ፤በቡና ካለሙት አስራ አንድ ሄክታር መሬት በየዓመቱ በአማካኝ እስከ 80 ኩንታል የእሸት ቡና ምርት እንደሚሰበስቡ ተናግረዋል።

ዘንድሮም 2ሺህ የቡና ችግኝ ለመትከል ማዘጋጀታቸውን ገልጸው  ለቡና ችግኙ እንክብካቤና ጥበቃ በማድረግ ተጠቃሚነታቸውን  ለማጠናከር ትኩረት መስጠታቸውን አስረድተዋል።

ቡናን በማልማት ልምድ ቢኖራቸውም ከምርምር ማዕከላት የተለቀቁ ዝሪያዎችን ስለማያገኙ የልፋታቸውን ያህል ተጠቃሚ እንዳልነበሩ የተናገሩት ደግሞ በወረዳው የብዲሞ ቀበሌ የልማቱ ተሳታፊ አቶ ሁሴን ሀሰን ናቸው፡፡

በአሁኑ ወቅት ግን ከመንግስት ያገኙትን የተሻሻሉ ዝሪያ ችግኞችን በመንከባከብ ለተከላ እያዘጋጁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አርሶ አደሮቹ እንዳሉት በአሁኑ ወቅት ከምርምር ተቋማት የወጡ አዳዲስ የቡና ዝሪያዎች በሽታን በመቋቋም ከነባሩ ዝሪያ በሄክታር ይገኝ የነበረውን 5 ኩንታል ከእጥፍ በላይ ማግኘት እንደሚችሉ ከባለሙያ በመረዳት  በስፋት ለማልማት ተዘጋጅተዋል፡፡

በባሌ ዞን በቡና ተክል ከተሸፈነው 51 ሺህ 391 ሄክታር ማሳ ውስጥ 26 በመቶ የሚሆነው የተፈጥሮ የጫካ ቡና መሆኑን ከዞኑ የእርሻና ተፈጥሮ ኃብት ልማት ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም