በያዮ ወረዳ በ15 ሚሊዮን ብር የንብ እርባታ ስልጠና ማእከል እየተገነባ ነው

112

መቱ፣ የካቲት 22/2013 /ኢዜአ/ በኢሉባቦር ዞን ያዮ ወረዳ ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የንብ እርባታ ስልጠና ማዕከል እየተገነባ መሆኑን የኦሮሚያ እንስሳት ሀብት ልማት ኤጀንሲ አስታወቀ።

የክልሉ የእንሰሳት ሀብት ልማት ኤጄንሲ ምክትል የቢሮ ኃላፊ አቶ ታመነ ባልቻ ለኢዜአ እንደገለጹት ምዕራብ ኦሮሚያ በተለይም የኢሉባቦር ዞን ካለው እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ጋር ተያይዞ ለማር ምርት ልማት ምቹና ከፍተኛ አቅም ያለው ነው ።

በአካባቢው ያለውን ምቹ ሁኔታና አቅም በመጠቀም የንብ እርባታ ስራን ለማዘመንና የማር ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ አቅጣጫ ተይዞ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል ።

በተያዘው አቅጣጫ መሰረት በኢሉባቦር ዞን ያዮ ወረዳ ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የንብ እርባታና የማር ምርት የስልጠና ማዕከል ግንባታ  እየተካሄደ መሆኑን አመልክተዋል ።

ማእከሉ በተለይም በእናት ንብ እርባታና በዘመናዊ የማር ምርት ልማት ለአርሶ አደሮች ስልጠና ከመስጠት በተጨማሪ በዘርፉ የጥናትና ምርምር ስራዎች የሚያካሂድ መሆኑን አመላክተዋል ።

የኢሉባቦር ዞን የእንስሳት ሀብት ልማት ኤጄንሲ ቢሮ ኃላፊ አቶ አወል መሐሙድ በበኩላቸው  በዞኑ ካለው የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ የደን ሀብት በተጨማሪ እስከ አንድ ሚሊየን የሚገመት የንብ መንጋ ይኖራል ተብሎ እንደሚታሰብ ጠቁመዋል።

"የእናት ንብ እርባታና የማር ምርት ልማት ስልጠና ማእከል ግንባታው ለአርሶ አደሮች ስልጠና፣ የሙያ ድጋፍና የምክር አገልግሎት ይሰጥበታል" ብለዋል።

ማእከሉ  የንብ ማነብ ሥራን በማዘመን ምርትን በመጠንና በጥራት በመጨመር ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አመላክተዋል።


በባህላዊ ዘዴ የንብ ማነብ ስራ ላይ የተሰማሩት አቶ ትንሣኤ ምትኩ የማዕከሉ መገንባት ለስራቸው ትልቅ ተስፋ እንደሆናቸው ገልፀዋል።

"ማዕከሉ ተጠናቆ ሥራ ሲጀምር በንብ ማነብ ስራየ ውጤታማ ለመሆን የሚያስችለኝን ተጨማሪ እውቀትና ድጋፍ አገኝበታለሁ የሚል ተስፋ አለኝ" ብለዋል።

"በባህላዊ ዘዴ ንብ በማነብ ማር ማምረት ከውጤቱ ይልቅ ድካሙ ትልቅ ነው" ያሉት ደግሞ አቶ ቀጭኔ ሾፌቦ ናቸው።

"እየተገነባ ያለው ማዕከል ድካማችንን እንደሚቀንሰውና ውጤታማ እንደሚያደርገን እምነት አለኝ" ብለዋል።

በምዕራብ ኦሮሚያ ማር በስፋት ከሚመረትባቸው ዞኖች የኢሉባቦር ዞን አንዱ ሲሆን በዞኑ በዓመት እስከ 25 ሺህ ቶን ማር እንደሚመረት ከዞኑ የእንስሳት ሃብት ልማት ኤጄንሲ የተገኘ መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም