በአማራ ክልል በልግ አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች 212 ሺህ ሄክታር መሬት ታርሶ በዘር እየተሸፈነ ነው - የክልሉ ግብርና ቢሮ

56

ባህር ዳር /ፍቼ የካቲት 22/2013 (ኢዜአ)- በአማራ ክልል የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ አካባቢዎች 212 ሺህ ሄክታር መሬት ታርሶ በዘር እየተሸፈነ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በያዝነው በልግ እርሻ  38ሺህ ሄክታር መሬት  በዘር እየተሸፈነ መሆኑን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ጽህፈት ቤት አስታውቋል ፡፡

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ኤልያስ በላይ ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ ሰሜንና ደቡብ ወሎ እንዲሁም ሰሜን ሸዋና የኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞኖች የምርት ወቅቱ እርሻ ተጀምሯል።

በዞኖቹ በምርት ወቅቱ ከ218 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት  በዘር ለመሸፈን ታቅዶ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል ።

እስካሁን ባለው ሂደት ታርሶ ከተዘጋጀው 212 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ 4ሺህ ሄክታሩ  በስንዴ፣ በገብስ፣ በቆሎ፣ በማሾ፣ በቀይ ጤፍና በጥራጥሬ ሰብሎች ዘር መሸፈኑን አመልክተዋል ።

በበልግ እርሻው 311 ሺህ አርሶ አደሮች የተሳተፉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

አርሶ አደሮቹ በበልጉ የሚጥለው አነስተኛ ዝናብ በእርሻ ማሳቸው ውስጥ እንዲቀር የውሃ ዕቀባ ስራ እንዲያከናውኑ በባለሙያዎች ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን አስታውቀዋል።

እንደ ባለሙያው ገለጻ በምርት ወቅቱ ከሚለማው መሬት  ከ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል።

በደሴ ዙሪያ ወረዳ የቀበሌ 36  ነዋሪ አርሶ አደር ጀማል ሙህዬ እየጣለ ያለውን ዝናብ በመጠቀም አንድ ሄክታር የሚሆን ማሳቸውን አርሰው በገብስና ስንዴ ዘር እየሸፈኑ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

ለምርት ወቅቱ የሚሆናቸው ማዳበሪያ ቀድሞ የቀረበላቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ግማሽ ሄክታር ማሳቸውን አለስልሰው ለዘር ማዘጋጀታቸውን የገለጹት ደግሞ በወረዳው የቀበሌ 41 ነዋሪ አርሶ አደር ተስፋሁን ከድር ናቸው፡፡

ዘንድሮ  ገብስና ስንዴ ለማልማት አቅደው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በክልሉ በ2012/13 ምርት ዘመን በበልግ ወቅት ከለማው 204 ሺህ 485 ሄክታር መሬት ከ2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በያዝነው በልግ ወቅት ለማልማት ከታቀደው ውስጥ 38ሺህ ሄክታሩ መሬት ታርሶ በዘር እየተሸፈነ መሆኑን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ጽህፈት ቤት አስታውቋል ፡፡

የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ መሳይ ወርቁ ለኢዜአ እንደገለፁት በዞኑ በልግ አብቃይ በሆኑ ሰባት ወረዳዎች  57 ሺህ ሄክታር መሬት  በዘር ለመሸፈን ታቅዶ ተግባራዊ እየተደረገ ነው።

በበልግ እርሻው ገብስ፣ ምስር፣ አተርና የቅባት እህሎች ትኩረት የተሰጣቸው መሆኑን ተናግረዋል።

እስካሁን  ባለው ሂደት ከ38 ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት ታረሶ በዘር በመሸፈን ላይ  መሆኑን አመልክተዋል ።

በበልግ እርሻው  ከ61 ሺህ የሚበልጡ አርሶ አደሮች የተሳተፉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

እንደ ሀላፊው ገለጻ በምርት ወቅቱ ከሚለማው መሬት ከ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል።

የደገም ወረዳ የቁንዴ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ድሪባ ፈይሶ በአካባቢው ለበልግ እርሻ አመቺ የሆነ የአየር ሁኔታ መኖሩን ጠቁመዋል።

"ዘንድሮ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ በተገቢው መንገድ በመጠቀም የተሻለ ምርት ለማግኘት አስበው የማሳ ዝግጅት እያካሄዱ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ  የግራር ጃርሶ ወረዳ የቶርባን አሼ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ብርሃኑ ደለሳ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም