የትራፊክ አደጋ ተጎጂዎች ፈጣን እርዳታ የሚያገኙበት መንገድ ሊመቻች ይገባል

90

የካቲት 21/2013 ዓም (ኢዜአ ) ህግ አስከባሪዎችና የጤና ባለሙያዎች የትራፊክ አደጋ ተጎጂዎች ፈጣን የህክምና አገልግሎት የሚያገኙበትን መንገድ ማመቻቸት እንደሚኖርባቸው ተገለጸ።

የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ ሁለት ሺህ ኪሎ ሜትር መንገዶች ላይ የመንገድ ደህንነት ዳሰሳ ጥናት በማድረግ ለአደጋ ተጋላጭ የሆነው 500 ኪሎ ሜትር መንገድ ላይ ማስተካከያ እንዲደረግ ለሚመለከተው አካል መተላለፉም ተገልጿል።

የትራፊክ አደጋ ተጎጂዎች ህክምና ከሚያገኙባቸው የህክምና ተቋማት ውስጥ አንዱ በሆነው አቤት ሆስፒታል በመገኘት ኢዜአ የትራፊክ አደጋ ተጎጂዎችን አነጋግሯል።

አቶ ደጀኔ አየለ በጉልበት ስራ እየተዳደሩ እንደነበረ ገልፀው በተሽከርካሪ ውስጥ እየተጓዙ ባሉበት ወቅት በደረሰባቸው አደጋ አንድ እግራቸውን ማጣታቸውን ተናግረዋል።

አቶ አለባቸው ተሰማ እና አቶ ምስለወርቅ አበራም ስለደረሰባቸው የትራፊክ አደጋ ተናግረዋል።

የትራፊክ አደጋ ተጎጂዎቹ በአደጋው የደረሰባቸው ጉዳት ለቀጣይ ህይወታቸው ፈተና እንደሚሆንባቸው ተናግረዋል።

የአቤት ሆስፒታል የህክምና ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር ሙሉጌታ ቦጋለ ለኢዜአ እንዳሉት ወደ ሆስፒታሉ የሚመጡት አብዛኛዎቹ ታካሚዎች በድንገተኛ አደጋ የሚመጡ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት በተሽከርካሪ አደጋና ተያያዥ አደጋዎች የሚመጡ ናቸው።

በትራንስፖርት ሚኒስቴር የብሄራዊ የመንገድ ደህንነት ምክርቤት ፅህፈት ቤት ኃለፊ አቶ ዮናስ በለጠ በበኩላቸው የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ "እንደርሳለን" በሚል በተጀመረው ዘመቻ የተለያዩ የግንዛቤ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።

ሚኒስቴሩ ከመንገድ ፈንድ ባገኘው በጀት የፍጥነት መቆጣጠሪያ ራዳሮች ገዝቶ ማከፋፈሉንና ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮችም በራሳቸው ገዝተው ቁጥጥሩን ለማጠናከር እየሰሩ መሆኑን አመልክተዋል።

ይህም በ2013 የመጀመሪያ መንፈቅ አመት በሰው ህይወትና አካል ላይ የደረሰው ጉዳት ከ2012 ግማሽ ዓመት ጋር ሲነፃፀር በተወሰኑ የክልል መስተዳድሮች አደጋው የመጨመር ሁኔታ ቢያሳይም በአገር አቀፍ ደረጃ ያለው ግን የመቀነስ አዝማሚያ ያሳየ ነው ብለዋል።

የሞት አደጋ በቁጥር 334 ወይም 15 በመቶ በላይ፣ ከባድ የአካል ጉዳት በቁጥር 774 ማለትም 23 በመቶ በላይ መቀነሱን ተናግረዋል።

ቀላል የአካል ጉዳት ግን በቁጥር በ567 ወይም28 በመቶ በላይ ጨምሮ የተገኘ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የትራፊክ ፖሊሶችንና የመንገድ ደህንነት ባለሙያዎችን አቅም ግንባታ ስልጠና ማግኘታቸውንና ከ2ሺህ ኪሎሜትር መንገዶች ላይ የመንገድ ደህንነት ዳሰሳ ጥናት ተደርጎ ለአደጋ አጋላጭ የሆኑት ተለይተዋል ብለዋል።

የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም