“ከአድዋ የበለጠ አንድ ሊያደርገን የሚችል ድል፣ ትግልና ሀሳብ የለም” -- ፖለቲከኞች

82

የካቲት 21/2013 (ኢዜአ) “ከአድዋ የበለጠ አንድ ሊያደርገን የሚችል ድል፣ ትግልና ሀሳብ የለም” ሲሉ የተለያዩ ፖለቲከኞች ተናገሩ።

በደምና በአጥንት በተከፈለ መስዋዕትነት ነጻነቷን አስከብራ የቆየችውን ኢትዮጵያን፣ ጀግኖች ልጆቿንና መሪዎቿን ማክበር ይገባልም ብለዋል።

አውሮፓዊያን በእነርሱ የዘመን አቆጣጠር በ1884 እና በ1885  በርሊን ላይ  ባደረጉት  ስምምነት የአፍሪካን የተፈጥሮ ሀብት ለመቀራመት፣ ለመዝረፍና ቅኝ ለመግዛት  ጦር አደራጅተው በመዝመት ብዙ ዝርፊያና ውድመት ፈፅመዋል፡፡

የነዚሁ አካል የሆነው የኢጣልያን ጦር የካቲት 23 ቀን  1888 ዓ.ም ኢትዮጵያን ለመውረር ያደረገው ሙከራ አድዋ ላይ በጀግኖች ኢትዮጵያዊያን ክንድ ከንቱ ሆኖ ቀርቷል፡፡

ይህን ተከትሎ ወራሪው ኃይል የሽንፈት ፅዋውን ሲቀምስ፤ የዓለም ታሪክ በበኩሉ  የኢትዮጵያዊያን ድል በጉልህ ጽፎታል።

ጀግኖች ኢትዮጵያዊያን በተባበረ ክንዳቸው እብሪተኛውን የኢጣልያ ጦርን ብቻ ሳይሆን የአውሮፓን የቅኝ ግዛት አስተሳሰብም የአድዋ ተራሮች ግርጌ ስር ቀብረውታል።

የድሉ ሚስጢር በመሪዎች ብልሃት፣ በድንቅ የጦር ስትራቴጂ፣ በኢትዮጵያዊያን ከብረት የጠነከረ አንድነት መገኘቱን ታሪክ ያወሳል።

የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችም አድዋ በአባቶቻችን እና እናቶቻችን የተባበረ ክንድ የተገኘ "ጥቁር  ሁሉ የኮራበት የጀግንነት ታሪክ ነው" ብለዋል።

“አንድነት ለጠላት እሾህ ነው” ያሉት የኢትዮጵያ ነፃነት ፓርቲ ሊቀ-መንበር አቶ ግዛቸው አበራ፥ የአድዋ ድል ኢትዮጵያዊያን ውስጣዊ ችግራቸው ሳይገድባቸው አንድ በመሆን አገራቸውን በማስቀደም በፈፀሙት ጀግንነት ይዘከራል ብለዋል።

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ሊቀ-መንበር አቶ ማሙሸት አማረ  በበኩላቸው  ጥቁር የሰው ዘር በሙሉ የሚኮራበት ድል የተመዘገበውና የኢጣልያ የሰለጠነ ጦር የተሸነፈው በኢትዮጵያዊያን የተባበረ ክንድ መሆኑን በማንሳት የአቶ ግዛቸውን ሀሳብ  ተጋርተዋል።

ከሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ወደ አድዋ የተመሙት ኢትዮጵያዊያን እውነተኛ ምክንያት፣ ፅኑ እምነት እና የአልደፈርም ባይነት ስሜት ይዘው ለመሞት ተዘጋጅተው መዋጋታቸውን ነው አቶ ማሙሸት ያወሱት ፡፡

“አድዋ የዘላለም ትምህርት ቤታችን ነው” ያሉት አቶ ግዛቸው የዚህ ዘመን ኢትዮጵያዊያን ልዩነትን ፣ አገርን ማስቀደምን፣ ውስጣዊ ችግርን  በውይይት መፍታት፣  ጠላትን  በጋራ መመከትን ከአድዋ ድል በመማር ሊተገብሩ ይገባል ብለዋል።

“ከአድዋ ድል የበለጠ አንድ ሊያደርገን የሚችል ድል፣ ትግልና ሀሳብ የለም” የሚሉት የመኢአዱ ሊቀ-መንበር አቶ ማሙሸት አማረ  እርስ በእርሳችን  ከመጓተት  ወጥተን  በአገር  ጉዳይ አንድ መሆንን ከአድዋ ጀግኖች እንማር ብለዋል።

“ኢትዮጵያ እንዴት እንደኖረች በማሰብ የተከፈለውን ዋጋ ወደድንም ጠላንም ማክበር ግድ ይለናል” ነው ያሉት፡፡

ፖለቲከኞቹ በአድዋ የተገኘውን ድል መሰረት በማድረግ በአስተሳሰብና በተቋም ደረጃ ጠንካራ የሆነችና ማንም የማይደፍራት አገርን መገንባት እንደሚገባም ነው የመከሩት።

የአድዋ ድል 125ኛ ዓመት በዓል ከየካቲት 1 ቀን 2013 ዓም ጀምሮ "የህብረ ብሔራዊ አንድነት ዓርማ " በሚል መሪ ሀሳብ በመላው አገሪቱ በተለያዩ ዝግጅቶች በመከበር ላይ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም