ራሱን 'ቄስ ወልደማርያም' እያለ የሚጠራው ሚካኤል በርሔ የኦርቶዶክስ ካህንም አማኝም አይደለም - ሊቀ ጳጳስ አባ ጴጥሮስ

259

የካቲት 20/2013 (ኢዜአ) ራሱን 'ቄስ ወልደማርያም' ነኝ ያለው ሚካኤል በርሔ ካህንም አማኝም እንዳልሆነ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በሰሜን አሜሪካ የኒውዮርክና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አባ ጴጥሮስ ገለጹ።

አባ ጴጥሮስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በሰሜን አሜሪካ የኒውዮርክና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ናቸው።

አባ ጴጥሮስ ለኢዜአ እንደገለጹት ከዚህ ቀደም በአውስትራሊያ በአገልግሎት ተመድበው ቆይተው በቅርቡ ወደ ሰሜን አሜሪካ ተዘዋውረዋል።

ሰሞኑን ራሱን "ቄስ ወልደማርያም" በማለት ሀሰተኛ መረጃ ያሰራጨው ሚካኤል በርሔ የተባለ ግለሰብ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አማኝም ካህንም እንዳልሆነ አረጋግጠዋል።

ሚካኤል በርሔ ሰሞኑን ራሱን "ቄስ ወልደማርያም" በሚል በለቀቀው የተንቀሳቃሽ ምስል በሕዳር 2013 ዓ.ም በአክሱም ጽዮን ቤተክርስቲያን በፀሎትና በቅዳሴ ላይ እያለን የተኩስ ድምጽ ሰማን፤ ስንወጣ "የአማራ ልዩ ሃይልና የኤርትራ ወታደሮች" እየተኮሱ ነበር ብሏል።

ሊቀ ጳጳሱ ደግሞ እርሳቸው ባሉበት ሀገረ ስብከት ውስጥም ይህ ግለሰብ እንደሌለ ጠቁመዋል።

እንደ እርሳቸው ገለጻ ግለሰቡ መኖሪያው ቦስተን ከተማ እንደሆነና በአንድ ሆስፒታል ውስጥ በአስተርጓሚነት እንደሚሰራ ሰምተዋል።

ከሁለት ሳምንት በፊት መቀሌ በነበሩበት ጊዜ ግለሰቡ ይህን ያህል ሰው አልቋል ብሎ የተናገረውን ሲሰሙ መደንገጣቸውን ነው የገለፁት። 

በተመሳሳይ መቀሌ በነበሩበት ወቅት ለጉብኝት የሄዱ የሃይማኖት አባቶች ተባረሩ የሚል መረጃ ሰምተው 'የት ነው ያለሁት' የሚል አግራሞት እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል። 

አባ ጴጥሮስ የሰሙት ነገር ከፍተኛ መደናገጥ እንደፈጠረባቸው ገልፀው "ውሸት ሲዋሽ እንኳ ትንሽ  ምክንያት ቢኖረው" ብለዋል።

"አንድን ነገር ስለጠላነው ወይንም ስለተቃወምነው ብቻ ከመሬት የለቀቀ ውሸት መዋሸት መጨረሻ ላይ የሚጎዳው ራስን ነው" ሲሉም አክለዋል።

ሀሰተኞች የሚበዙት ሰሚ ስላገኙና ለምን ብሎ የሚጠይቅ ባለመኖሩ መሆኑን የተናገሩት ሊቀ ጳጳሱ ሕዝቡም እውነትን ከያዙ ሰዎች ጋር በእውነት እንዲሰራ መክረዋል።

ይህ ሰው ይህን ውሸት ስለተናገረ ለአክሱም ሕዘብ ምንም እንደማይጠቅመውና ለራስ፣ ለአገርና ለወገን ሲባል ከውሸት ቢቆጠብ መልካም ነው ብለዋል።

"ይህ ሰውዬ አክሱም አልነበረም፣ የቤተክርስቲያኒቱ ካህን አይደለም፣ በቤተክርስቲያኒቱም አያገለግልም፣ ክህነት በሚባለው ነገርም አያገለግልም" ነው ያሉት።

ሚካኤል በርሄ ይህን ሁሉ ያልሆነውን ነኝ ብሎ ከተናገረ ከዚህ የባሰ ውሸት እንደሚዋሽ ሁሉም ሰው ሊያውቅና ሊጠነቀቅ ይገባል ብለዋል።

መገናኛ ብዙሃንም እንደዚህ አይነት ግለሰቦች መረጃዎችን ከማበላሸታቸው በፊት ተጨባጭ መረጃዎችን ለኅብረተሰቡ ማስተላለፍ እንደሚገባቸውም አቡነ ጴጥሮስ አሳስበዋል።

ቄስ ወልደማርያም ነኝ በማለት የሚንቀሳቀሰው ሚካኤል በርሔ በለቀቀው የተንቀሳቃሽ ምስል በአክሱም ጽዮን ቤተክርስቲያን በፀሎትና በቅዳሴ ላይ "የአማራ ልዩ ሃይልና የኤርትራ ወታደሮች" እየተኮሱ ነበር በሚል ሀሰተኛ መረጃው ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ለማደናገር መሞከሩ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም