"ወጣቶች ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር ስብዕናቸውን መፈተሸ አለባቸው" - ዶክተር ወዳጄነህ ማኀረነ

58

የካቲት 20/2013 (ኢዜአ) ወጣቶች ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር ተሳትፎ ማድረግ ብቻ ሳይሆን የተሳትፎው ባለቤት መሆን እንዳለባቸው ተጠቆመ።

ወጣቶች ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር ስብዕናቸውን መፈተሸ እንዳለባቸውም ተነግሯል።

"የወጣቶች ሠላማዊ ተሳትፎ ለብሔራዊ መግባባትና ለመጪው ምርጫ" በሚል ዐቢይ ርዕስ ውውይት ተካሂዷል።

መርሃ ግብሩን ዓለምአቀፍ የማነቃቃት አገልግሎት ድርጅት ያዘጋጀው ሲሆን ተጋባዥ እንግዶች በብሔራዊ መግባባት ዙሪያ ንግግር አድርገዋል።

ወጣት ምሁራንና የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ ወጣቶች፣ የመንግሥት የስራ ሃላፊዎችና የወጣት ማኅበራት ተወካዮች በውይይቱ ተሳትፈዋል።

የብሔራዊ መግባባትና ፖሊሲ ጥናት ተመራማሪው ዶክተር ብርሃኑ ሌንጂሶ ባደረጉት ንግግር ወጣቶች ብሔራዊ መግባባት ለማምጣት መሳተፍ ብቻ ሳይሆን የተሳትፎው ባለቤት መሆን አለባቸው ብለዋል።

ወጣቶች ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር በተለያዩ ዘርፎች ተሳትፎ ማድረግ እንዳለባቸው በማመልከት በብዛት የፖለቲካ ሁነቶችና ልማት ላይ ብቻ ሲሳተፉ መስተዋሉን ጠቁመዋል።

የአፍሪካዊያን ተሞክሮም ይህን እንደሚያሳይ በመግለፅ ወጣቶች በተለይ በግብርናው ዘርፍ ያላቸው አስተዋፅኦ መዳከሙን ተናግረዋል።

የወጣቶች ልማት ከኢኮኖሚና ከፖለቲካ የሰፋ መሆን እንዳለበትና 'አካላዊና አዕምሯዊ ብሎም የሥነ ልቦናና መንፈሳዊ መነቃቃት ከማኅበራዊ ተሳትፎ ጋር ያስፈልጋቸዋል' ነው ያሉት።

ማኅበራዊ ተሳትፎ ሲያድግ ወጣቱ ለአገሩ እንደሚሰራና የጋራ መግባባት ላይ እንደሚደርስ ነው ዶክተር ብርሃኑ የተናገሩት።

'በአገራችንም ወጣቶች የፖሊሲ ግንባታ ላይ ምን ያህል አስተዋፅኦ አላቸው እና ፖለቲካን እንዴት ነው የሚመለከቱት የሚሉትን ማጤን ያስፈልጋል' ብለዋል።

በተለይም ከ1960ዎቹ የወጣቶች የፖለቲካ ተሳትፎና ውጤቱ በኋላ "ፖለቲካና ኮረንቲ በሩቁ" የሚለውን ሀሳብ በመተው ወጣቶችን ማሳተፍ የግድ መሆኑን አሳስበዋል። 

በኢትዮጵያ 70 በመቶ የሚሆነው ወጣት እንደሆነና አገሪቷም ትልቁ ሀብቷ ወጣቱ የኅበረተሰብ ክፍል በመሆኑ በውስጧ ያለውን ድህነትና ተቃርኖ ለማስወገድ ከፍተኛ ድርሻ አለው ብለዋል።

'ታሪካችንን መለስ ብለን ስናይ አባቶቻችን ብዙ መልካም ነገር አውርሰውን ነገር ግን ተወያይቶ መግባባትን ባለመውረሳችን አገራዊ መግባባት ላይ ለመድረስ ወጣቶች ላይ እንስራ' ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

የውይይቱ ተሳታፊ የነበሩት ዶክተር ወዳጄነህ ማኀረነ በበኩላቸው "ወጣቶች ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር ስብዕናቸውን መፈተሸ አለባቸው" ብለዋል። 

ስሜታቸው፣ ሀሳባቸውና ባህሪያቸው ተደምረው በገነቡት ስብዕናቸው ላይም መሥራት ይኖርባቸዋል ሲሉ መክረዋል።

"የልጅነትን ንቃትና በዕድሜ የገፉ አባቶችን ብስለት አጣምረው የሚሄዱት ወጣቶች ናቸው" ያሉት ኡስታዝ አቡበከር አህመድ ደግሞ ወጣቱ የጋራ መግባባት ለመፍጠር 'እኔ ማነኝ' ብሎ መጠየቅ አለበት ነው ያሉት።

"ታሪክ የማይሰራ ትውልድ ባለፈው ታሪክ ይጣላል" ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ፕሬዚዳንት ፓስተር ፃድቁ አብዶ ሲሆኑ ይህ ሀሳብ ሃገሪቷን እየጎዳት ነው" ብለዋል።

ስለሆነም ወጣቱ ብሔራዊ መግባባት ላይ ለመድረስ የራሱን ታሪክ ተባብሮ መስራት አለበት ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም