ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ 47 የሰብል እና የእንስሳት ዝርያዎችን በምርምር በማውጣት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረጉን ገለጸ

83

ሐረር፤ የካቲት 20/ 2013 (ኢዜአ) ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ 47 የሰብል እና የእንስሳት ዝርያዎችን በምርምር በማውጣት ከ62ሺ በላይ የማህበረሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ማድረጉን ገለጸ።

ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች በመጀመሪያ፣ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸው  ተማሪዎችን  ዛሬ አስመርቋል።

በምረቃው ሥነ-ሥርዓት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት  ዶክተር ጀማል ዩስፍ  እንደገለጹት  ተቋሙ ከመማር ማስተማር ስራው በተጓዳኝ በቴክኖሎጂ  ምርምር እና  ማህበረሰብ  አገልግሎት ላይ በትኩረት እየሰራ  ይገኛል።

ዩኒቨርሲቲው እስካሁን ባደረገው እንቅስቃሴ ችግር ፈቺ የሆኑ 109  የምርምር ስራዎችን ማጠናቀቁንና 229 በሂደት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በዩኒቨርሲቲውና ለሌሎች የምርምር ተቋማት የተገኙ 47 የሰብል እና  የእንስሳት  ዝርያዎችን አላምዶ በማውጣት ከ62ሺህ የማህበረሰበ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረጋቸውን   ዶክተር ጀማል ገልጸዋል።

የዕለቱ የክብር እንግዳ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር  ሳሙኤል  ክፍሌ በበኩላቸው  የአሁኑ ትውልድ የአድዋን ድል ሲያከብር መማር ያለበት ኢትዮጵያዊ ወንድማማችነት እና ህብረት ወደ ታላቅ ስኬት እንደሚወስድ ነው ብለዋል።

ዛሬ ላይ ድህነትን፣ጥላቻን፣ግለኝነትን እና ሌብነትን በወንድማማችነትና በህብረት በማሸነፍ ፣ ሰላም ፣ፍቅርና መቻቻልን የሰፈነበት የበለጸገኝ ኢትዮዽያን እውን ማድረግ ይጠበቅብናል ብለዋል።

ተመራቂዎችም ይህንን በመገንዘብ የሀገሪቱን የብልጽግና ጉዞ ለማሳካት በሚደረገው  እንቅስቅሴው ውስጥ በመሳተፍ የድርሻቸውን እንዲወጡ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በሁለተኛ ዲግሪ  የተመረቀው  አንያብ አኔቦ በሰጠው  አስተያየት የኮሮና ቫይረስ በመማር ማስተማሩ ላይ ተጽዕኖ ቢያሳድርም በህብረተሰቡና መንግስት ድጋፍ አጠናቀን ለምረቃ በቅተናል ብሏል።

በተማረው የሙያ መስክ ውጤታማ ሰራን በማከናወን ህብረተሰቡን ለማገልገል ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል።

በተማርኩበት መያ ህዝቤን ለማገልገል በቁርጠኝነት እሰራለሁ ያለችው ደግሞ ሌላዋ ተመራቂ ሊዲያ አለማየሁ ናት።

ሊዲያ ባስተላለፈችው መልዕክትም ሁላችንም በአንድነት፣ በመተባባር እና በኢትዮጵያዊነት ስሜት ምንም ዓይነት መጣጠል ሳይኖር ሀገራችንን ማሳደግ አለብን ብላለች።

ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ዛሬ  ካስመረቃቸው ተማሪዎች መካከል 21 በዶክትሬት እና 385  ደግሞ በሁለተኛ ዲግሪ የተማሩ ይገኙበታል።

ተመራቂዎቹ የሰለጠኑት በግብርና፣ አካባቢ ሳይንስ፣ አግሮ ኢንዱስትሪና መሬት ሃብት፣ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ እና  የጤና ማህበረሰብ ሳይንስና በሌሎችም የትምህርት መስኮች  መሆኑ ተመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም