ሰብዓዊ ድጋፉ ችግራችንን ከማቃለል ባለፈ ተረጋግቶ ለመኖር ያግዘናል-- በአክሱም ድጋፍ የተደረገላቸው ነዋሪዎች

አክሱም የካቲት 20/2013 (ኢዜአ) ከመንግስት የሚደረግላቸው ሰብዓዊ ድጋፍ ችግራቸውን ከማቃለል ባለፈ ተረጋግተው ለመኖርና ልጆቻቸውን ለማሳደግ እንደሚያግዛቸው በትግራይ ማዕከላዊ ዞን አክሱም ከተማ ድጋፍ የተደረገላቸው ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

የማዕከላዊ ዞኑ አስተዳደር በበኩሉ በዞኑ በርካታ ወረዳዎች ለሚገኙ ነዋሪዎች ሰብዓዊ ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ የጸጥታ ስጋት ባለባቸው ቦታዎችም ድጋፉን ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች በሕግ ማስከበሩ ወቅት በርካታ ችግሮችን ማሳለፋቸውን ገልጸው በአሁኑ ወቅት መንግስት ለችግራቸው እየደረሰላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመንግስት እየተደረገላቸው ያለው ሰብዓዊ ድጋፍ የራሳቸውንም ሆነ የልጆቻቸውን ሕይወት እየታደገላቸው እንደሚገኝ ነው የተናገሩት፡፡

በሰብዓዊ ድጋፉ ለአንድ ግለሰብ ለሁለት ወር የሚሆን 30 ኪሎ ግራም ስንዴ፣ 5 ኪሎ ማካሮኒ እና ለሚያጠቡ እናቶችና ለልጆቻቸው የወተት ድጋፍ መደረጉን አስተያየት ሰጪዎቹ ገልጸዋል፡፡  

ድጋፉን ከማግኘታቸው በፊት በችግር ውስጥ እንደነበሩ የተናገሩት ነዋሪዎቹ፤ የተደረገላቸው ድጋፍ ለአንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን እስከሚቋቋሙ ድረስ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የማዕከላዊ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኔ ገብረጻዲቅ ሰብዓዊ ድጋፉ መጀመሪያ ቢዘገይም በአሁኑ ወቅት በአድዋ፣ አክሱም፣ ላዕላይ ማይጨውና ሌሎች የገጠር አከባቢዎች መዳረሱን ገልጸዋል፡፡

ከማዕከላዊ ዞን አንዳንድ አካባቢዎች ተፈናቅለው በአክሱም ከተማ ለሚገኙ ወገኖችም ሰብዓዊ ድጋፍ መድረሱን አክለዋል፡፡

በዞኑ የጸጥታ ስጋት በሚስተዋልባቸው የገጠር አካባቢዎች በመከላከያ ሠራዊት እጀባ ድጋፉን ለማድረስ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች በመንግስትና በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ትብብርከ ሰብዓዊ ድጋፍ እየተዳረሰ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም