በኦሮሚያ ክልል በስድስት ወራት 17 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ገቢ ተሰበሰበ

87

አዳማ፤ የካቲት 20/2013(ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያው ስድስት ወራት 17 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።

የጨፌ ኦሮሚያ 5ኛ የጨፌ የሥራ ዘመን 6ኛ ዓመት 13ኛ መደበኛ ስብሰባ በአዳማ ገልማ አባገዳ መሰብሰቢያ አዳራሽ እየተካሄደ ነው።

የስድስት ወሩ በክልሉ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊና በፖለቲካ መስክ የተከናወኑ ስራዎችን  አፈጻጻም በተመለከተ አቶ ሽመልስ ለጨፌ ኦሮሚያ ሪፖርት አቅርበዋል።

በሪፖርቱም በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት በክልሉ ከተለያዩ የገቢ ምንጮች 17 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን ገልፀዋል።

በግማሽ ዓመቱ ከመደበኛ ገቢ 13 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 15 ነጥብ 3  ቢሊዮን ብር የተሰበሰበ ሲሆን ይህም የዕቅዱ 111 በመቶ  መሆኑም ተጠቅሷል።

ከማዘጋጃቤታዊ ገቢ 2 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር  ገቢ መገኘቱና አፈፃፀሙ ከዕቅዱ 86 ነጥብ 2 በመቶ መሆኑን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፤  የተገኘው ገቢ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ5 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር  ጭማሪ  እንዳለውም አስታውቀዋል።

በክልሉ የሚሰበሰበውን ገቢ ለማሳደግ የተሰሩ የንቅናቄ ሥራዎች በግማሽ ዓመቱ  የተገኘው ገቢ እንዲጨምር ከፍተኛ ሚና መጫወቱንም አቶ ሽመልስ በሪፖርታቸው  ጠቅሰዋል።

በክልሉ ኢንቨስትመንት ለመሳብ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመው፤  በዚህም ባለሃብቶች በክልሉ መዋዕለንዋያቸውን እያወጡ ነው ብለዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት 86 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሀብቶች እንዲሁም ለ 4 ሺህ 385 ፕሮጀክቶች ፈቃድ መሰጠቱን ነው የገለጹት። 

በተጨማሪም በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ለነበሩ ፕሮጀክቶች ድጋፍ በማድረግ ዳግም ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉን አክለዋል።

በክልሉ የአገልግልት አሰጣጥን በማሻሻል ከሕዝብ የሚቀርበውን ቅሬታ ለመፍታት  በትኩረት እየተሰራ  ነው ብለዋል።

ከቱሪስት ዘርፍ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ ዕቅድ ተይዞ ወደሥራ መገባቱንም  ጠቁመዋል። 

መጪው አገራዊ ምርጫ ስኬታማ እንዲሆን የክልሉ መንግስት በትኩረት እንደሚሰራም  የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፤በክልሉ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሠላማዊ መንገድ  በመንቀሳቀስ ወደ ኅብረተሰቡ እንዲደርሱ የክልሉ መንግስት የበኩሉን እገዛ  እንደሚያደርግም  አረጋግጠዋል።

ከዚህ በተቃራኒ በክልሉ የሕዝቡን ሠላም ለማደፍረስና ሕዝቡን ለማደናገር በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድም ተናግረዋል።

የጨፌ ኦሮሚያ መደበኛ ስብሰባ እንደቀጠለ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም