የአድዋ ድል በትምህርት ስርዓት ተካቶ ትውልድ ለማነፅና የአገር ግንባታ ከሚመራባቸው ጉዳዮች አንዱ የመሆን አቅም አለው

79

አዲስ አበባ፤ የካቲት 19/2013(ኢዜአ) የአድዋ ድል የትምህርት ስርዓቱ አካል ሆኖ ትውልድ ለማነፅና የአገር ግንባታ ሂደት ከሚመራባቸው ጉዳዮች አንዱ የመሆን አቅም እንዳለውም ተገለፀ።

በአንድነት በመቆም ከውጭ የተቃጣ ጥቃት የተመከተበት የአድዋ ድል ኅብረት ችግሮችን ለመሻገር መሰረት መሆኑን እንደሚያስገነዝብም የሠላም ሚኒስቴር ገልጿል። 

በአገሪቷ ዘላቂ ሠላም ለማምጣት የሚያከናውናቸውን ተግባራት አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ያስታወቀው ሚኒስቴሩ "አድዋ ለለውጣችን የጋራ ድላችን" በሚል መሪ ሃሳብ አምባሳደሮች፣ ዲፕሎማቶችና የዓለም አቀፍ ድርጅት ተወካዮችን በማሳተፍ 125ኛውን የአድዋ ድል አስመልክቶ የምክክር መድረክ ተካሂዷል።

በመድረኩ "የአድዋ ድል ዘመናዊ የመገናኛ መሳሪያና የተሟላ የመሰረተ ልማት ባልነበረበት ወቅት በርካቶችን ለጦርነት በማሰባሰብ ድል የተገኘበት አኩሪ ገድል" ስለመሆኑ ተገልጿል።

የአድዋ ድል የኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆን የመላው ጥቁር ሕዝብ የድል ታሪክና የቅኝ ገዥዎችን ታሪክ ጭምር የቀየረ መሆኑም ተመላክቷል።

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ምክትል ሊቀመንበር ኩዌሲ ኳርቲ የአድዋ ድል ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካ የነፃነት ተምሣሌት ነው ብለዋል።

የአድዋ ድል በአንድነት የተባበሩ ሕዝቦች ያሰቡትን እንደሚያሳኩ ማሳያ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

የሠላም ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል በበኩላቸው አድዋ ለኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆን ለመላው ነፃነትና ፍትህ ወዳድ ሕዝብ በሙሉ ትርጉም የሚሰጥ ድል መሆኑን ተናግረዋል።

"ከብሄር፣ ከሃይማኖትና ከጾታ ልዩነት በመራቅ በአንድነት በመቆም የተገኘው የአድዋ ድል አንድነት ማንኛውንም ችግር መሻገር እንደሚያስችል ማሳያም ነው" ብለዋል ሚኒስትሯ።

ይህን ታሪክ ቀምሮ ለትውልድ ለማስተላለፍ መሰራት እንዳለበትም አመልክተዋል።

መድረኩ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የአድዋን ድል ታሪክና ከሠላም አኳያ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን እንዲገነዘብ የተሰናዳ መሆኑን ተናግረዋል።

አድዋ የትምህርት ስርዓቱ አካል ሆኖ ትውልድ እንዲታነፅበትና የአገር ግንባታ ሂደት ከሚመራባቸው ጉዳዮች አንዱ የመሆን አቅም እንዳለውም ገልጸዋል።

ሚኒስቴሩ ዘላቂ ሠላም ለማረጋገጥ በርካታ ተግባራትን እየከወነ መሆኑንና ላለፉት ሁለት ዓመታት የጥናትና ምርምር ስራዎች ሲካሄዱ መቆየታቸውን አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ ለጎረቤት አገራትና ለዓለም ሠላም የምትቆም እንደሆነች ገልፀው፤ አሁንም ከጎረቤት አገራት ጋር ያለውን ችግር በሠላም መፍታት እንደምትሻ ገልፀዋል።

125ኛው የአድዋ ድል በዓል "አድዋ የኅብረ ብሔራዊ አንድነት ዓርማ" በሚል መሪ ሃሳብ እየተከበረ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም