የሶማሌ ክልል ዳያስፖራ አባላት የመጀመሪያ ክልላዊ ውይይት በጅግጅጋ እየተካሄደ ነው

87

የካቲት 19/2013(ኢዜአ) የሶማሌ ክልል ዳያስፖራ አባላትን ሁለንተናዊ ተሳተፎ የማሳደግ ዓላማ ያለው የመጀመሪያው ክልላዊ የዳያስፖራ ውይይት በጅግጅጋ እየተካሄደ ነው።

በውይይቱ ላይ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ከሦስት ሚሊዮን በላይ የዳያስፖራ አባላት አሏት።

በአፍሪካ ከናይጄሪያ ቀጥላ ሁለተኛዋ ሰፊ ቁጥር ያላት ስትሆን፤ ኢትዮጵያዊያን የዳያስፖራ አባላት በትውልድ አገራቸው ላይ ያላቸው ተሳተፎ በየጊዜው አያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።

"የዳያስፖራ አባላት የሬሚታንስ፣ የንግድና ኢንቨስትመንት አቅማቸውን አገራቸው ላይ ማዋል ጀምረዋል፤ የክህሎት፣ የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖርም ሚናቸው የጎላ ሆኗል" ብለዋል።

ኢትዮጵያዊያን ዳያስፖራዎች ባለፉት ስድስት ወራት ከ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ወደ አገራቸው ማስገባት እንደቻሉም ጠቁመዋል።

በተጨማሪም በ3 ሺህ 186 አዳዲስ የሂሳብ ቁጥሮች ከ4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር በላይ መቆጠብ ተችሏል ብለዋል።

"ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከ89 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ መሰብሰብ ችለዋል፤ 847 የዳያስፖራ አባላትም የኢንቨስትመንት ፈቃድ እንዲሰጣቸው ተደርጓል" ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ የዳያስፖራ አባላትን ተሳትፎና ንቅናቄ በዘላቂነት ለማሳደግ ከጎናቸው ሆኖ እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።

የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ኤልያስ አብዱላሂ በበኩላቸው "አብዛኛው ሰው ስደት ሲባል ቀድሞ የሚያስታውሰው አሉታዊ ተጽዕኖውን ብቻ ነው" ብለዋል።

"ይሁን እንጂ በየትኛውም ዓለም ያሉ ዳያስፖራዎች በአገራቸው ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ጉልህ አዎንታዊ አስተዋጽኦ አላቸው" ሲሉ ጠቅሰዋል።

የዳያስፖራ አባላት በአገራቸው ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ አጋር ሆነው እየሰሩ መሆናቸውንም ነው የገለጹት።

በዚህም ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ብቻ በዓለም ላይ አነስተኛና መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት የሄዱ የዳያስፖራ አባላት ወደ አገራቸው የሚልኩት የውጭ ምንዛሬ በሦስት እጥፍ ማደጉን ጠቁመዋል።

ይህም እንደ አውሮፓዊያኑ የዘመን ቀመር 2019 የዳያስፖራ አባላት ሬሚታንስ ወደ 550 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ማለቱን ገልጸዋል።

"ይሄም የተቀባይ አገራትን የቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲሁም የልማት አጋዥነት ከፍተኛ እንደሆነ ማሳያ ነው" ብለዋል።

የሶማሌ ክልል ዳያስፖራ አባላት የሚልኩት የውጭ ምንዛሬ የክልሉን 30 በመቶ አጠቃላይ ምርት እንደሚሸፍንና ለአገሪቷ እድገትም የማይናቅ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

የውይይት መድረኩ በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲና በሶማሌ ክልል ኢንቨስትመንትና ዳያስፖራ ቢሮ ትብብር የተዘጋጀ ነው።

በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ እ.አ.አ ከ2019 ጀምሮ ለሁለት ዓመታት በሙከራ ደረጃ ሥራ የጀመረው የሶማሌ ክልል ዳያስፖራ አባላት ተሳትፎ ፕሮግራም የአባላቱን ተሳትፎ ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም