የጋፋታ ኢንዱስትሪ መንደር እሳቤ መከላከያ ለደረሰበት ዘመናዊ አደረጃጀት መሰረት ጥሏል--አቶ አገኘሁ ተሻገር

123

የካቲት 19/2013 (ኢዜአ) በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው የጋፋት ኢንዱስትሪ መንደር እሳቤ አሁን ላይ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ለደረሰበት ዘመናዊ አደረጃጀት መሰረት መሆኑን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር አስታወቁ።

የጋፋት የኢንዱስትሪ መንደር መልሶ ማቋቋም ፕሮጀክት የጋራ ስምምነት ትናንት  በደብረ ታቦር ከተማ አቅራቢያ በምትገኘው ፍሩይ አባረጋይ ቀበሌ ተካሄዷል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በፊርማ ስነ ስርዓቱ ላይ እንዳሉት አጼ ቴዎድሮስ ከውጭና ከውስጥ የተነሱባቸውን ጠላቶች በጋፋት የጦር መሳሪያዎችን በማምረት የሀገር አንድነትን ለማስጠበቅ የጣሩ ታላቅ መሪ ነበሩ።

"በዚያ ዘመን የተጀመረውን ስልጣኔ ማስቀጠል ባለመቻሉ ሀገራችን በከፋ ድህነትና  ኋላቀርነት ስትማቅቅ እንድትኖር ተገዳለች" ብለዋል።

አሁን ላይ በመከላከያ ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን እየተካሄደ ያለው ተግባርና ዘመናዊ የሰራዊት ግንባታ የጋፋትን እሳቤና አሻራ መሰረት ያደረገና የጥንቱን ስልጣኔ ለመመለስ የሚያስችል መሆኑን አመልከተዋል።

 "በጥንታዊው የጋፋት የጥበብ መንደር የተጀመረው ፕሮጀክት ታሪክንና ተግባር የተገናኘበት ነው" ሲሉም ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ የመላው ኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች በመሆኑ የሀገሪቱን የቀጣይ ብልጽግና በሚያረጋግጥ መልኩ እንዲፈጸም የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አሰታውቀዋል።

የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር ዲኤታ አቶ ፍስሃ ወልደ ሰንበት  በበኩላቸው  በቅርቡ  በተካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻ የአማራ ክልል ልዩ ሃይልና ሚሊሻ ከመከላከያ ጎን በመሰለፍ ለፈጸሙት ተጋድሎና ላስመዘገቡት አኩሪ ድል ምስጋና አቅርበዋል።

 የመከላከያ ተቋም ለውጡን ተከትሎ ሀገራዊና ህዝባዊ ጥቅምን የሚያስጠብቅና  የጠላትን  እኩይ ፍላጎት አስቀድሞ ለመግታት የሚያስችል ማሻሻያ እያካሄደ መሆኑን  ገልጸዋል።

ተቋማዊ ማሻሻያው የመከላከያ ሰራዊቱን በቴክኖሎጂ የማዘመንና  የማስታጠቅ  ዓላማን  ሰንቆ እየተተገበረ መሆኑን ጠቁመው ጋፋት የቴክኖሎጂው አንዱ አሻራ በመሆኑ ለፕሮጀክቱ ውጤታማነት ተቋሙ ሃላፊነቱን እንደሚወጣ አረጋግጠዋል።

 “የጋፋት ኢንዱስትሪ መንደር መልሶ ማቋቋም ፕሮጀክት የሀገራችን የብልጽግና መሰረት የሆነውን የታሪክ ምዕራፍ ለመክፈት የሚያስችል ነው” ያሉት ደግሞ የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ  አቶ ቀለመወርቅ ምህረቴ ናቸው።

"አጼ ቴዎድሮስ በዘመነ መሳፍንት የነበረውን መከፋፈል በማስወገድ የኢትዮጵያን አንድነት ማስጠበቃቸው ለአሁኑ ትውልድ አርአያ ያደርጋቸዋል" ብለዋል።

አጼ ቴዎድሮስ ኢትዮጵያን በሳይንስና ቴክኖሎጂ ለማዘመን ካላቸው  ፍላጎት  የተነሳ  በጋፋት  የጥበብ መንደር አንድ ግዙፍና ስምንት  ትንንሽ መድፎችን  በራስ  አቅም  በማምረት በተግባር ያዋሉ መሪ እንደነበሩ አውስተዋል።

አሁን ላይ ስምምነት የተደረሰበት የጋፋት ኢንዱስትሪ መንደር መልሶ ማቋቋም ፕሮጀክት የሀገሪቱን የብልጽግና መሰረት የሆነውን የታሪክ ምዕራፍ  ለመክፈት  የሚያስችል  መሆኑን አመልክተዋል።

"ጋፋት ኢትዮጵያ ከመንደር ፖለቲካ አስተሳሰብ ወጥታ ልእለ ሃያልነትን እንድታማትር ያደረገ ቦታ በመሆኑ አሁን ላይ የመከላከያ ሰራዊት ሀገርን ከብተና ለማዳን እየፈጸመ ላለው ተጋድሎ ትልቅ አቅም ነው" ብለዋል።

"የፕሮጀክቱ ዋና ዓላማ የጋፋትን ታሪካዊነት በመጠበቅ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ማዕከል ማድረግ ነው "ያሉት ደግሞ የደብረ ታቦር ዩኒቨርስቲ  ፕሬዚዳንት  ዶክተር  አነጋግረኝ ጋሻው ናቸው።

"አጼ ቴዎድሮስ አካባቢውን ለኢንዱስትሪ የመረጡት በወቅቱ የብረት ሙያተኞች የሚገኙበት፣ የብረት ማዕድን ያለበትና አካባቢው ለግዛታቸው ማዕከል በመሆኑ ነው" ብለዋል።

"ፕሮጀክቱ የአጼ ቴዎድሮስን ራእይ ለማሳካት ወሳኝ ነው" ያሉት   ፕሬዝዳንቱ የጋፋት  መንደርን በጥናት ላይ የተመሰረተ የኢንዱስትሪና የሳይንስና ቴክኖሎጂ ማዕከል ለማድረግ እንደሚሰራ አመላክተዋል።

ዩኒቨርሲቲው ለአካባቢው ነዋሪዎች ካሳ በመክፈል ከ 2 ነጥብ 8 ሄክታር በላይ  መሬት  ከመከለልና ከመጠበቅ ባሻገር ከ5 ሚሊየን ብር በላይ ወጭ በማድረግ መዳረሻ መንገድ ማሰራቱን ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል።

የጋፋት ኢንዱስትሪ መንደር መልሶ ማቋቋም ፕሮጀክት ስምምነት በደብረታቦር ዩኒቨርስቲ፣ በደቡብ ጎንደር ዞን አስተዳደርና በመከላከያ ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ተፈርሟል።

በፊርማ ስነ ስርዓቱ ላይ የክልሉና የጎንደር ዞኖች አመራሮች፣ የመከላከያ ተወካዮች፣ የአካባቢው ማህበረሰብና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም