ትውልዱ የህዳሴ ግድብን ዳር ለማደረስ መረባረብ እንዳለበት የህዳሴ ቱር አሰተባባሪ ተናገሩ

91

ድሬዳዋ የካቲት 19/2013( ኢዜአ) የአሁኑ ትውልድ የህዳሴ ግድብን ዳር በማድረስ እንደ አድዋ ድል ታሪክ ለመስረት መረባረብ እንዳለበት የህዳሴ ቱር አስተባባሪና የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ባህልና ቅርስ አድን ድርጅት ዋና ዳይሬክተር አቶ አማሃ አለሙ ተናገሩ።

የህዳሴ ቱር አባላት በድሬዳዋ ተገኝተው ለግድቡ ህዝባዊ የድጋፍ ቅስቀሳ አድርገዋል፡፡

አቶ አማሃ አለሙ ከትናንት ማምሻው ጀምሮ በነባራቸው የቅስቀሳ ወቅት ለሀገር ሁለንተናዊ ብልጽግና ዕውን መሆን መሶሶ የሆነው የህዳሴ ግድብ እየተገባደደ መሆኑ ያስደስታል ብለዋል፡፡

ትውልዱ ይህን የሀገር ኩራት ተረባርቦ ከዳር በማድረስ  እንደ ታላቁ የአድዋ ድል ታሪክ ለመስራት መረባረብ  እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

በየደረጃው የሚገኘው ህዝብ በገንዘብ፣ ዕውቀትና ሃሳብ በመደገፍ የግድቡ ባለቤት የሆነበት ግድብ ግንባታ  ዳር ለማድረስ  ቦንድ በመግዛት፣ በ8100 መልዕክት በመላክ ተሣትፎውን እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የህዳሴ ቱር አባላት ዛሬም ህዝብ በሚበዛባቸው ዋና ዋና አደባባዮች ፣ ጎዳናዎችና  ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ተገኝተው ቅስቀሳ አድርገዋል፡፡

የድሬዳዋ አሰተዳደር የህዳሴ ግድብ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ተወካይ አቶ ወጋየሁ ገበየሁ በበኩላቸው የድሬዳዋ ነዋሪ ለግድቡ በስጦታና በቦንድ ግዢ ከ85 ሚሊዮን ብር በላይ በማዋጣት ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዋል፡፡

ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ከአርቲስቶችና ቅርስ ባለአደራ የተውጣጡት የህዳሴ ቱር አባላት ድሬዳዋ ካሄዱት ቅስቀሳ በህዝቡ ውስጥ መነቃቃት የሚፈጥር ከመሆኑም በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ያግዛል ብለዋል፡፡

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የ80 ዓመቱ አዛውንት አቶ ሽመልስ ተመስገን በሰጡት አስተያየት ልክ ለአደዋ ጀግኖች የሚሰጠው ክብርና ሞገስ ግድቡን ለምናከናውነው ለአሁኑና  መጪው ትውልድ በተመሣሣይ ክብር ይሰጠናል ብለዋል፡፡

ለህዳሴው ግድብ ድጋፍ እንዲውል ሶስት ጊዜ ባንድ መግዛታቸውንና እንደሚቀጥሉበትም ገልጸው  ሁሉም ዜጋ ለግድቡ ዳር መድረስ እንዲደገፍ  መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የከዚራ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ አኒሳ አብዲ በበኩሉ ግድቡ ለሀገር እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው በመሆኑ ከቤተሰብ ከሚሰጠው በመቆጠብ  ቦንድ መግዛቱን እንደሚቀጥል ተናግሯል፡፡

በኢትዮጵያ ታሪክ ፣ባህልና ቅርስ አድን ድርጅት ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ጋር በመተባበር የተዘጋጀው የህዳሴ ቱር ሉኡካን  ድሬዳዋን ጨምሮ በሀገሪቱ 29 የተለያዩ ከተሞች ላይ ተመሣሣይ ቅስቀሳ ማድረጉንና አሁን ላይ ለተመሳሳይ ተግባር ወደ ሐረር ማቅናቱ ተመልከቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም