በማረሚያ ቤቶች ሰብዓዊ መብቶችን በማክበርና በማስከበር የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን እየተሰራ ነው -- ኮሚሽኑ

59

የካቲት 19/2013 (ኢዜአ) በማረሚያ ቤቶች የታራሚዎችን ሰብዓዊ መብት በማክበርና በማስከበር የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ስራ እየተሰራ መሆኑን የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ገለጸ።

በማረሚያ ቤት የሰብአዊ መብት አያያዝ ላይ ያተከረው 12ኛው የፌዴራልና የክልል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽነሮች ጉባዔ ትናንት በአዳማ መካሄድ ጀምሯል።

የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽነር ጄኔራል ጀማል አባሶ እንዳሉት የታራሚዎችን መብት ለመጠበቅ የተቋሙን የማቋቋሚያ አዋጅ ማሻሻልን ጨምሮ የተለያዩ ደንብና መመሪያዎች ተዘጋጅተው ሥራ ላይ እንዲውሉ ተደርጓል።

ለአዋጁና መመሪያዎቹ ተግባራዊነትም ለሠራተኞች ተከታታይ የሥራ ላይ ስልጠና በመስጠት በአመለካከት፣ በእውቀትና በክህሎት ለውጥ እንዲመጣ መደረጉን ጠቁመዋል።

የማረሚያ ቤቶችን ሠላምና ደህንነት በማረጋገጥ የታራሚዎችን ሰብዓዊ መብት አክብሮ በማስከበር የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ እየተደረገ መሆኑን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።

የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ምክትል ዓቃቤ ሕግ አቶ አድማሱ አንጎ "የአገሪቱ ኢኮኖሚ በሚፈቅደው ልክ የታራሚዎች መሰረታዊ ፍላጎት እንዲሟላ በትኩረት መስራት ይገባል" ብለዋል።

ታራሚዎችን ለማነጽ የሚሰጡ ትምህርትና ስልጠናዎችን በማስፋፋት የእውቀትና ክህሎት ባለቤት እንደሆኑ ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል።

ይህም ታራሚዎች ቅጣታቸውን ጨርሰው ወደኅብረተሰቡ ሲቀላቀሉ አምራችና ሕግ አክባሪ ዜጋ እንዲሆኑ ስለሚያስችል ትኩረት እንዲሰጠው አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ በበኩላቸው በተለያዩ ማረሚያ ቤቶች መሻሻሎች መኖራቸውን አንስተዋል።

ይሁንና በፖሊስ ጣቢያና በአንዳንድ ክልሎች የሙያ ስነ ምግባራቸውን በማያከብሩ አባላት የመብት ጥሰት ሲፈጸም እንደሚስተዋል ጠቁመዋል።

ኮሚሽኑ በክልል ማረሚያ ቤቶችና ፖሊስ ጣቢያዎች ድንገተኛ ጉብኝት ለማድረግ በሚሄድበት ጊዜ በር የመዝጋት ሁኔታ ስለሚስተዋል ይህ እንዲታረም አሳስበዋል።

"የፍትህ ስርዓቱን ለማሻሻል የሚደርገውን ጥረት ለማገዝ ቢሮው ቁርጠኛ ነው" ያሉት ደግሞ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአደንዛዥ እፅ እና ወንጀል ቢሮ በኢትዮጵያ ተወካይ ማርጋሬት አኩሎ ናቸው።

በጉባዔው የማረሚያ ቤቶች የሰብዓዊ መብቶች አያያዝና የስድስት ወራት አፈጻጸምን በሚመለከት መነሻ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል።

የክልልና የከተማ አስተዳደር ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽነሮች፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ ጠቅላይ ዓቃቤ ህግና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትን ጨምሮ የዓለም ዓቀፍ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎችና ተወካዮች ጉባዔውን ታድመዋል።

ጉባዔው በለውጥ መርህ በተቃኘ አስተሳሰብና በሙያዊ ስነ ምግባር በመታገዝ የሕግ ታራሚዎችን የሰብዓዊ መብት አያያዝ፣ የማረምና የማነፅ አገልግሎት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ያለመ ነው ተብሏል።

"ማረሚያ ቤቶች የሕግ ታራሚዎች ሰብዓዊ መብቶች የተከበሩባቸው ተቋማት እንዲሆኑ ተግተን እንሰራለን"  በሚል መሪ ሀሳብ ትናንት የተጀመረው ጉባዔ ዛሬ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም