የባቡር ሃዲድ ብረቶችን በመቁረጥና በመፍታት ስርቆት የፈፀመው ግለሰብ የቅጣት ውሳኔ ተላለፈበት

389

አዳማ፤ የካቲት 19/201 (ኢዜአ) በምስራቅ ሸዋ ዞን ሉሜ ወረዳ የባቡር ሃዲድ ብረቶችን በመፍታትና በመቁረጥ ስርቆት የፈፀመው ግለሰብ በእስራትና ገንዘብ እንዲቀጣ የተወሰነበት መሆኑን ፖሊስ አስታወቀ።

የዞኑ ፖሊስ መምሪያ የኮሙዩኒኬሽንና ሚዲያ ሃላፊ ኮማንደር አስቻለው ዓለሙ  እንደገለጹት ግለሰቡ በሉሜ ወረዳ  ቲሲቄ ቀበሌ  በተለያዩ ጊዜያት  ነባሩን የባቡር ሃዲድ ብረቶች በመፍታትና በመቆራረጥ ዘረፋ ሲፈጽም እንደቆየ በምርመራ ተረጋግጦበታል።

መሃመድ አባተ የተባለው ይሄው ግለሰብ  ከግብረ አበሮቹ ጋር በመሆን የካቲት 13/ 2013 ዓ.ም. ከለሊቱ 9 ሰዓት  ደግሞ  የታርጋ ቁጥሩ ኮድ 3- 80256 አ.አ. በሆነ አይሱዙ እና  ኮድ 3- 61468 አ.አ. ኤፍ ኤስ አር የጭነት ተሽከርካሪዎች የዘረፈውን የባቡር ሃዲድ ብረቶች ጭኖ ለመሰወር ሲሞክር በፖሊስ  በቁጥጥር ስር  መዋሉን አመልክተዋል።

ጉዳዩን የተመለከተው የምስራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የግለሰቡ ድርጊት  በሰውና ሰነድ ማስረጃ በማረጋገጥ  የካቲት 16/06/2013 ዓ. ም. በዋለው ችሎት በ3 ዓመት እስራትና የ4 ሺህ ብር ቅጣት የወሰነበት መሆኑን  ኮማንደር አስቻለው አለሙ ለኢዜአ ገልጸዋል።

ግብረ አበሮቹ ለጊዜው ቢያመልጡም ለመያዝ ክትትል እየተደረገባቸው መሆኑንም አመልክተዋል።

በቅርቡም በምስራቅ ሸዋ ዞን  በቦሰት ወረዳ ጠዴቾ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ውስጥ  ዘጠኝ ግለሰቦች በሌሊት የባቡር ሀዲድ ብረት ሲዘርፉ በቁጥጥር ስር እንደዋሉ በወቅቱ ዘግበናል።