የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት በመተከልና ትግራይ ክልል ለሚገኙ ዜጎች ድጋፍ አደረጉ

87

አዲስ አበባ፣ የካቲት 18/ 2013 ዓ.ም የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት በቤኒሻንጉል ክልል መተከል ዞን እና በትግራይ ክልል ለሚገኙ ዜጎች ድጋፍ አደረጉ።

በትግራይ ክልል በሕግ ማስከበር በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ባለው ግጭትና የጸጥታ ችግር ንጹሃን ዜጎች ድጋፍ እንደሚሹ ይታወቃል።

በጣይቱ ሆቴል "ሰብዓዊነትና ፍቅር፤ ለትግራይና መተከል" በሚል መሪ ሃሳብ ጉዞ አድዋ፣ ለትግራይ እርዳታ አሰባሰብ በጎ ፈቃደኛ፣ አለም ዓቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት፣ የኢትዮጵያ በጎ ፈቃደኛ ጋዜጠኞች እና የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብቶች ማህበር በጋራ ድጋፍ ማሰባሰብ 15 ቀናትን አስቆጥሯል።

የድጋፍ ጥሪውን ተከትሎም በአገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የገንዘብ፣ የአልባሳት የምግብ እና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ እያደረጉ ይገኛል።

የድጋፉ አስተባባሪና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ታማኝ በየነ ዛሬ የትራንስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ያኒያ ሰይድመኪ በመተከልና ትግራይ ክልል ለሚገኙ ዜጎች የአንድ ወር ደመወዛቸውን መለገሳቸውን ገልጿል።

የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ፍሬህይወት ሽባባው በግላቸው 100 ሺህ የሚያወጣ የምግብ አቅርቦትና የንጽህና መጠበቂያዎችን ድጋፍ ማድረጋቸውንም እንዲሁ።

ባለስልጣናቱ ያደረጉት ድጋፍ ለኢትዮጵያዊያን ወገኖቻቸው ተቋርቆሪና አሳቢ መሆናቸውን በተግባር አሳይተዋል ብሏል።

ሌሎችም የመንግስት ባለስልጣናት ለወገኖቻቸው ድጋፍ በማድረግ አጋርነታቸውን ሊያሳዩ እንደሚገባ ተናግሯል።

በአገር ውስጥና በውጭ አገር የሚገኙ ዜጎች አሁንም ለትግራይና መከተከል የሚያደርጉት ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉን ነው ታማኝ በየነ የገለጸው።

አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ሂደት ከተጠናቀቀ በኋላ የተሰባሰበውን ድጋፍ የማከፋፈል ስራ እንደሚጀመርም ጠቁሟል።ሰብአዊ ድጋፍ እያደረጉ ለሚገኙ ተቋማትና ግለሰቦች ከነገ በስቲያ የምስጋና መርሃ ግብር እንደሚካሄድም አስታውቋል።

ለወገኖቹ ድጋፍ ማድረግ ለሚሻ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሁሉ በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ስም በተከፈተ የሒሳብ ቁጥር “1000327016559” ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ ቀርቧል።LikeCommentShare

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም