የአገሪቷን ሕግ በማያከብሩ ዓለምአቀፍ መገናኛ ብዙሃን ላይ የእርምት እርምጃ ይወሰዳል - የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን

57

አዲስ አበባ፣ የካቲት 18 /2013 ዓ.ም (ኢዜአ)   ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ትግራይ ክልል ገብተው የሚዘግቧቸው ዘገባዎች ትክክለኛና ሃቀኛ እንዲሁም የጋዜጠኝነትን አስተምህሮ የተከተሉ ሊሆኑ እንደሚገባ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን አሳሰበ።

ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃኑ ሕገ-መንግስቱን ጨምሮ ሌሎች የአገሪቷን ሕጎች ሳያከብሩ ሲሰሩ ከተገኙ በሕግ አግባብ እርምጃ እንደሚወሰድባቸውም ገልጿል።

መንግሥት ትናንትና ቢቢሲ እና ሮይተርስን ጨምሮ ሰባት ዓለም አቀፍ የሚዲያ ተቋማት በትግራይ ስላለው ሁኔታ መዘገብ እንዲችሉ ፈቃድ መስጠቱን አስታውቋል።

ከቢቢሲ እና ሮይተርስ በተጨማሪ በመጀመሪያው ምዕራፍ የክልሉን ሁኔታ መዘገብ እንዲችሉ የተፈቀደላቸው የሚዲያ ተቋማት ኤ.ኤፍ.ፒ፣ አልጀዚራ፣ ኒው-ዮርክ ታይምስ፣ ፍራንስ-24 እና ፋይናንሺያል ታይምስ ናቸው።

ይህን ተከትሎ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን በምን መልኩ መዘገብ አለባቸው በሚለው ዙሪያ የባለስልጣኑ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ወንድወሰን አንዱአለም ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃኑ ከዚህ ቀደም ትግራይ ክልል ገብተው ሊዘግቡ ያልቻሉት የየብስና የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ተቋርጦ ስለነበርና በሁኔታዎች አለመመቸት ነው ብለዋል።

ይህን ተከተሎ አንዳንድ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ወደ ክልሉ ገብተው መስራት ባለመቻላቸው የተዛባ ዘገባ የሚሰሩት መረጃ ማግኘት ስላልቻሉ እንደሆነ ለባለስልጣኑ ሲገልፁም ነበር ነው ያሉት።

አሁን አብዛኛው የሕግ ማስከበር ስራ በመገባደዱና የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችም ራሳቸውን ለአደጋ ሳያጋልጡ መዘገብ የሚችሉበት ሁኔታ ስለተፈጠረ ወደ ክልሉ ገብተው እንዲዘግቡ መወሰኑን ገልፀዋል።

ሆኖም ወደ ክልሉ ገብተው እንዲዘግቡ ሁኔታዎች ሲፈቅዱ አንዳንድ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ወደቦታው ሄደው ለመዘገብ እንደማይሹ እየገለፁ መሆኑን ጠቁመዋል።

እንደ አቶ ወንድወሰን ገለጻ ይህ ከዚህ ቀደም የተዛባ መረጃ ሲያቀርቡ የነበሩት የፖለቲካ ፍላጎት፣ የጥቅም ግጭት እንዲሁም በውጭ ተልዕኮ ግፊት እንደሆነ ማሳያ ነው።

በክልሉ ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች እየተደረገ ያለውን ጥረት ከመዘገብ ይልቅ ከእውነት የራቀና የተጋነነ እንዲሁም ግጭት አባባሽ ዘገባዎች ሲሰሩ እንደነበረም አስረድተዋል።

ባለስልጣኑ በመገናኛ ብዙሃኑ ዘገባዎች ላይ ቁጥጥር /ሚዲያ ሞኒተሪንግ/ ሲያደርግ ከአገሪቷ የብሮድካስት አዋጅ፣ ከሕገመንግስቱ፣ ከሰብዓዊ መብት ድንጋጌና ከጋዜጠኝነት አስተምህሮ ያፈነገጠ ዘገባ ሲሰሩ የነበሩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን መኖራቸውን መገንዘቡንም ጠቅሰዋል።

ባለስልጣኑ ይህን ተከትሎ ባለሙያዎቹን እየጠራ ሲያናግር እንደነበርና እነሱም በዚያ ወቅት ስህተት እንደፈፀሙ ማመናቸውን አቶ ወንድወሰን ገልፀዋል።

መገናኛ ብዙሃን ውግንናው ለእውነትና ለፍትህ ሊሆን እንደሚገባ ገልፀው ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃኑ ከሕግ አግባብ ውጭ የሚሰሩ ከሆነ ግን ባለስልጣኑ በሕግ አግባብ የእርምት እርምጃ ለመውሰድ ይገደዳል ብለዋል።

ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃኑ የመንግስትና የባለስልጣኑ ዝምታና ትዕግስት ለሙያው ካለ ክብርና ቀናኢነት የመነጨ መሆኑን በመገንዘብ ሠላማዊ፣ ትክክለኛና ሃቀኛ ዘገባዎችን ሊሰሩ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም