ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ የአምባሳደሮችና የዲፕሎማቶቿን ትጋት የምትሻበት ጊዜ ነው

67

አዲስ አበባ፣ የካቲት 18/2013 ( ኢዜአ) ኢትዮጵያ ያለችበት ነባራዊ ሁኔታ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ የአምባሳደሮችና የዲፕሎማቶቿን ትጋትና ውጤታማነት የምትፈልግበት መሆኑ ተገለጸ።


ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ አዲስ ተሿሚ አምባሳደሮችን በብሔራዊ ቤተ-መንግስት የስራ መመሪያ በመስጠት ሽኝት ያደረጉላቸው ሲሆን አምባሳደሮቹ ቃለመሃላ ፈፅመዋል።

ፕሬዚዳንቷ "አገርን በልብ ብቻ ሳይሆን በድርጊቶቻችሁ ሁሉ ይዛችሁ እንደምትንቀሳቀሱ ለአፍታም መዘንጋት የለባችሁም" ሲሉ አዲሶቹን አምባሳደሮች አሳስበዋል።

አምባሳደርነት አገርን ተሸክሞ የመሄድ ከፍተኛ ሃላፊነት ነው ያሉት ፕሬዚዳንቷ በተለይም ድሃ አገርን ወክሎ የሚሄድ አምባሳደር ከተመደበበት አገር ሊገኝ የሚችልን ጥቅም አሟጦ መጠቀም እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ዲፕሎማሲን እንደ ወቅቱ የዓለም ተጨባጭ ሁኔታ ማዛመድ እንደሚያስፈልግ ገልጸው አምባሳደር ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን የተመደበበትን አገር ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ታሪክና ባህል በአግባቡ ሊያውቅ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያን ገጽታ ለመገንባት ከመቼውም ጊዜ በላይ መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመው ለዚህም በተለያዩ አገራት የተመደቡ አምባሳደሮች ድርብ ሃላፊነት አለባቸው ብለዋል።

አገርን ማስተዋወቅ የአምባሳደር ቀዳሚ ተግባር ነው ያሉት ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ የአምባሳደርነትን ሚና ከአክቲቪዝም መለየት እንደሚገባ አሳስበዋል።

አምባሳደር ሲሾም ሕዝብና መንግስት ከፍተኛ ሃላፊነት ሰጥተውት እንደመሆኑ አገር ከሰጠው ተልዕኮ ውጭ በሌላ ተግባር መሰማራት እንደሌለበትም አስገንዝበዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በበኩላቸው አምባሳደርነት በውጭ ግንኙነት መስክ የአገር ብሄራዊ ጥቅሞች በተቀባይ አገር ዘንድ እንዲረጋገጡ ለማድረግ የሕዝብና የመንግስት ሃላፊነትና ተልዕኮ የሚወሰድበት ከፍተኛ የስልጣን እርከን መሆኑን አውስተዋል።

አምባሳደር በተወከለበት አገር መልካም የመንግስት ለመንግስት፣ የሕዝብ ለሕዝብና የተቋማት ግንኙነት በመፍጠር ወደ ተጨባጭ ግንኙነት እንዲጎለብት አበክሮ መስራት አለበትም ብለዋል።

ኢትዮጵያ ያለችበት ነባራዊ ሁኔታ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ የአምባሳደሮችና የዲፕሎማቶቿን ትጋትና ውጤታማነት የምትሻበት ነው ያሉት አቶ ደመቀ አምባሳደሮቹ በሚመሯቸው ሚሲዮኖች ተገቢውን የአመራር ሚና በመጫወት ተልዕኳቸውን በአግባቡ እንዲወጡ አሳስበዋል።

ቃለ መሃላ ከፈፀሙ አምባሳደሮች መካከል በአውስትራሊያ የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሙክታር ከድር፣ በጣሊያን ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ደሚቱ ሀምቢሳ፣ በቱርክ የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር አደም መሐመድ ይገኙበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም