በሰው ማገት ወንጀል የተከሰሰ ግለሰብ በአስር ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ተወሰነበት

79

ጎንደር ፤የካቲት 18/2013(ኢዜአ) በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ታች አርማጭሆ ወረዳ በሰው ማገት ወንጀል የተከሰሰ ግለሰብ በአስር ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ የተወሰነበት መሆኑን የወረዳው ፍርድ ቤት አስታወቀ፡፡

ፍርድ ቤቱ የእሰራት ቅጣቱን ያስተላለፈው የሳንጃ ከተማ ነዋሪ የሆነው አይንሸት አጥናው በተባለ ግለሰብ ላይ ነው፡፡

ግለሰቡ በወረዳው ያይራ በተባለው ቀበሌ በከብት ጥበቃ ላይ የነበረን ታዳጊ ወጣት ሌሎች ለጊዜው ካልተያዙ ግብረ አበሮቹ ጋር በመሆን ነሐሴ/ 2012 ዓ.ም. የሰው እገታ ወንጀል መፈጸሙን የፍርድ ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ጌታሁን አበጀ ለኢዜአ ገልጸዋል።

ግለሰቡ ያልተገባ ጥቅም በመፈለግ ታዳጊ ወጣቱን አፍኖ ጫካ በመውሰድ ለሶስት ቀናት እገታ በመፈጸም ከቤተሰቦቹ 40ሺህ ብር ተቀብሎ እንደለቀቀው በህግ ምስክሮች የተረጋገጠበት መሆኑን ተናግረዋል።

ባለሙያው እንዳሉት ተከሳሹ ወንጀሉን አልፈጸምኩም በማለት ክዶ ቢከራከርም የቀረበበትን ማስረጃ ማስተባበል ባለመቻሉ ጥፋተኛ ተብሏል።

ግለሰቡ ከዚህ ቀደም የወንጀል ሪከርድ የሌለበትና የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆኑን ፍርድ ቤቱ ግምት ውስጥ አስገብቶ በቅጣት ማቅለያነት ይዞለት ሰሞኑን በዋለው ችሎት ከተያዘበት ጊዜ ጀምሮ የሚታሰብ በአስር ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ እንደተወሰነበት አስታውቀዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ከሁለት ወራት በፊት በሰው ማገት ወንጀል በተከሰሰ ሌላ ግለሰብ ላይ የ15 ዓመት ጽኑ እስራት ውሳኔ ማሳለፉን ባለሙያው አስታውሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም