ሉሲዎቹ በዛሬው የሴካፋ የሴቶች እግር ኳስ ውድድር ታንዛኒያን ካሸነፉ ዋንጫ ያነሳሉ

82
አዲስ አበባ ሐምሌ 20/2010 ሉሲዎቹ በዛሬው የሴካፋ የሴቶች እግር ኳስ ውድድር ታንዛኒያን ካሸነፉ ዋንጫ ያነሳሉ። በሩዋንዳ እየተካሄደ ያለው ሶስተኛው የምስራቅና መካከለኛው ምስራቅ (ሴካፋ) የሴቶች እግር ኳስ ውድድር ዛሬ ፍጻሜን ሲያገኝ የውድድሩ የመጨረሻ ጨዋታዎች ይደረጋሉ። ከሐምሌ 12 ቀን 2010 ዓ.ም አንስቶ ሲካሄድ የቆየው ይህ ውድድር ኢትዮጵያን ጨምሮ አዘጋጇ ሩዋንዳ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳና ታንዛኒያ በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ። በስታድ ደ ኪጋሊ ስታዲየም ዛሬ ከቀኑ 9 ሰአት የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከታንዛኒያ ከቀኑ 11 ሰአት ከ 15 ደቂቃ አዘጋጅ አገር ሩዋንዳ ከኬንያ ጋር ይጫወታሉ። በአጠቃላይ በውድድሩ ላይ የሚሳተፉ አገራት እርስ በእርስ በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች የተሻለ ነጥብ ያስመዘገበ ቡድን የውድድሩ አሸናፊ ይሆናል። የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በመጀመሪያ ጨዋታው በኡጋንዳ ቢሸነፍም ቀጣይ ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች አዘጋጇ ሩዋንዳንና ኬንያን በማሸነፍ በስድስት ነጥብና በሶስት የግብ ክፍያ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል። ሁሉንም ጨዋታ ያደረገው የኡጋንዳ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በሰባት ነጥብና በአንድ የግብ እዳ የመጀመሪያ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። በአሰልጣኝ ሰላም ዘርአይ አሰልጣኝነት የሚመሩት ሉሲዎቹ ታንዛንያን ካሸነፉ የሴካፋ ሴቶች እግር ኳስ ውድድር የዋንጫ ባለቤት መሆናቸውን ያረጋግጣሉ። የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን አቻ ከተለያየ የውድድሩ አሸናፊ ለመሆን ሩዋንዳ ከኬንያ አቻ ወጥተው ወይም ኬንያ በሩዋንዳ ከ5 የጎል ልዩነት በታች መሸነፍ አለባት። በሂሳባዊ ስሌት ሲታይ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከሌሎቹ አገራት ብሔራዊ ቡድኖች አንጻር ሰፊና የተሻለ እድል አለው። አራት ነጥብና ሁለት የግብ ክፍያ ያላት ታንዛንያ ኢትዮጵያን ከአንድ ጎል በላይ በሆነ ልዩነት ካሸነፈች የውድድሩ አሸናፊ የመሆን እድል አላት። አራት ነጥብና ሁለት የግብ እዳ ያለባት አዘጋጅ አገር ሩዋንዳ ሉሲዎቹ ተሸንፈው ሩዋንዳ ኬንያን በአምስት ጎል ልዩነት ካሸነፈች የውድድሩ አሸናፊ የመሆን እድል ይኖራታል። ኢትዮጵያ የሴካፋ የሴቶች እግር ኳስ ውድድርን ካሸነፈች ለመጀመሪያ ጊዜ ይሆናል። በኡጋንዳ ከአራት ዓመት በፊት በተካሄደው የሴካፋ እግር ኳስ ውድድር የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ሉሲዎች አዘጋጇ ኡጋንዳን አራት ለአንድ በሆነ ሰፊ ውጤት በማሸነፍ ሶስተኛ ደረጃን ይዘው ያጠናቀቁበት ከፍተኛ ያስመዘገቡት ውጤታቸው ነው። የሴካፋ ሴቶች እግር ኳስ ውድድር እ.አ.አ በ1986 ለመጀመሪያ ጊዜ ሲካሄድ ዛንዚባር ውድድሩን ያሸነፈች ሲሆን ከሁለት ዓመት በፊት በኡጋንዳ በተካሄደው ውድድር ታንዛንያ አሸናፊ መሆኗ ይታወሳል። በሌላ ዜና የፋሲል ከተማ እግር ኳስ ክለብ ሶስት ተጫዋቾችን ያስፈረመ ሲሆን ሀብታሙ ተከስተ፣ በዛብህ መለዮና ሽመክት ጉግሳ ክለቡ ያስፈረማቸው ተጫዋቾች ናቸው። የአማካይ ተጫዋዎቹ ሀብታሙ ተከስተ ከመቀሌ ከተማ፣ የክንፍ መስመር ተጫዋቹ ሽመክት ከደደቢትና የአጥቂ ክፍል ተጫዋቹ በዛብህ መለዩ ከወላይታ ዲቻ ነው የፈረሙት። ሶስቱም ተጫዋቾች የሁለት ዓመት ኮንትራት መፈራረማቸውን ከክለቡ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። በተጨማሪም ፋሲል ከተማ የኮንትራት ውሉ ሰኔ 30 ቀን 2010 ዓ.ም የተጠናቀቀውን የተከላካይ ክፍል ተጫዋች ሰኢድ ሀሰንን ለተጨማሪ ሁለት ዓመታት ውሉን እንዲያራዝም አድርጓል። ክለቡ ግብ ጠባቂው ቴዎድሮስ ጌትነት፣ የመሐል ክፍል ተጫዋች መጣባቸው ሙሉና የግራ መስመር ተጫዋቹ አምሳሉ ጥላሁን ውላቸውን በሁለት ዓመት እንዲራዘም ማድረጉ የሚታወስ ነው። የመጀመሪያ ዙር የአገር ውስጥ የተጫዋቾች ዝውውር ሐምሌ 10 ቀን 2010 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን የዝውውር መስኮቱ የ2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እስከሚጀመርበት ቀን እንደሚቆይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል። የመጀመሪያ ዙር የውጪ ተጫዋቾች ዝውውር ደግሞ ከሐምሌ 5 ቀን እስከ ጥቅምት 13 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ ይቆያል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም