በዞኑ 136 ሺህ በጎ ፈቃደኞች የበጋ ወቅት አገልግሎት እየሰጡ ነው

71

ደሴ የካቲት 17/2013 ( ኢዜአ) በደቡብ ወሎ ዞን 136 ሺህ በጎ ፍቃደኞች የበጋ ወቅት አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን የዞኑ ሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ መምሪያ አስታወቀ፡፡

በመምሪያው የወጣቶች ማካተት ንቅናቄና ተሳትፎ ቡድን መሪ አቶ ምስጋናው ደምሴ ለኢዜአ እንደገለጹት በዞኑ ከመስከረም 2013 ዓ.ም መጀመሪያ ጀምሮ የበጋ ወቅት በጎ ፍቃድ አገልግሎት እየተሰጠ ነው ።

የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራ፣ የአቅመ ደካማ ሰዎች ሰብል ስብሰባና መኖሪያ ቤት ጥገና፣ የደም ልገሳ ፣  የአንበጣ መንጋና ኮረናን መከላከል የመሳሰሉ አገልግሎቶችን እየሰጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በጎ ድቃደኞቹ እስካሁን ባከናወኑት አገልግሎት የ4 ሺህ የአቅመ ደካማና በህግ ማስከበር ተግባር የተሰማሩ የጸጥታ አባላት ሰብል መሰብሰቡን አመልክተዋል ።

በአንድ ሺህ ተፋሰሶች ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ መሰራቱንና ከ1 ሺህ 600 ዩኒት በላይ ደም  መሰብሰቡን ለአብነት ጠቅሰዋል ።

በቃሉ ወረዳ የቀበሌ 022  ነዋሪ ወይዘሮ ዘይነባ አሊ በበኩላቸው ባለቤታቸው ህግ በማስከበር ዘመቻ በመሄዳቸው  በአንድ ሄክታር ማሳ ላይ የለማ የማሽላና የጤፍ ሰብል በበጎ ፍቃደኛ ወጣቶች  አማካኝነት የተሰበሰበላቸው መሆኑን ተናግረዋል ።

"ስለፋ የከረምኩበት ሰብል ሳይሰበሰብ ሊቀርነው ብዬ ስጨነቅ ወጣቶች በወቅቱ ስለሰበሰቡልኝ ተደስቻለሁ" ብለዋል፡፡

በኮምቦልቻ ከተማ የቀበሌ 03  ነዋሪ ወጣት ቢኒያም የሱፍ  በበጋ በጎ ፍቃድ በመሳተፍ ለህብረተሰቡ እየሰጠ ባለው አገልግሎት የህሊና እርካታ ማግኘቱን ገልጻል ።

ጓደኞቹን በማስተባበር በቃሉ ወረዳ የአቅመ ደካማ አርሶ አደሮችን ሰብል የመሰብሰብና የአንበጣ መንጋ የመከላከል አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን ተናግሯል ።

በኮምቦልቻ ከተማ ወጣቱን አስተባብረው ከ100 ዩኒት በላይ ደም እንዲሰበሰብ ማድረጋቸውንም ወጣት ቢኒያም ገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም