የሙያ ማኅበራት ኢኮኖሚው የሚፈልገውን ክሕሎት የተላበሰ የሰው ሃይል የማፍራት ጥረት ሊደግፉ ይገባል

63

የካቲት16/2013 (ኢዜአ ) የሙያ ማኅበራት መንግስት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የሚፈልገውን ክሕሎት የተላበሰ የሰው ሃይል ለማፍራት የሚያደርገውን ጥረት እንዲያግዙ ተጠየቁ።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በከፍተኛ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ከተለያዩ የሙያ ማኅበራት ፕሬዚዳንቶች ጋር ተወያይቷል።

የሙያ ማኅበራቱ በከፍተኛ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ዘርፍ ሊኖራቸው በሚገባው ሚና ላይ ምክክር ተካሂዷል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዲኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ እንደተናገሩት በቀጣዮቹ ዓመታት እንደ አገር ለማሳካት የተያዙ ዕቅዶችን እውን ለማድረግ ከፍላጎት ጋር የተናበበ ባለሙያ ማፍራት ያስፈልጋል።

ለዚህ ደግሞ የሙያ ማኅበራት በየዘርፎቻቸው ለትምህርት ጥራትና አግባብነት መረጋገጥ የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።    

ሚኒስቴሩም የከፍተኛ ትምህርት ጥራትና አግባብነትን ለማረጋገጥ የ10 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ አዘጋጅቶ ወደ ተግባር መግባቱን ተናግረዋል።

የውይይት መድረኩ ዓላማ የሙያ ማኅበራቱ በከፍተኛ ትምህርት ጥራትና ተገቢነት መስክ ሚናቸውን እንዲወጡ የሚያደርግ የጋራ አቋም ለመያዝ ነው ብለዋል።

እስካሁን ማኅበራቱና መንግስት በትምህርት ዘርፍ ተናበውና ተመጋግበው መስራት ባለመቻላቸው እንደ አገር ለሚስተዋለው የትምህርት ጥራት መጓደሎች ምክንያት መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የሙያ ማኅበራት በከፍተኛ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ወሳኝ ሚና ያላቸው መሆኑንም ገልፀዋል።

ከእነዚህም መካከል በስርዓተ ትምህርት ቀረጻ መሳተፍ፣ የፕሮግራሞችና የአገልግሎቶችን ደረጃ ማውጣት፣ በምዘና አሰጣጥ ስራ መሳተፍና ተከታታይ የሙያ ዕድገት ስልጠና ማዘጋጀትን ዘርዝረዋል።

የሙያ ማኅበራቱ እነዚህንና መሰል ተግባራትን በመከወን መንግስት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የሚፈልገውን ክሕሎት የተላበሰ የሰው ሃይል ለማፍራት የሚያደርገውን ጥረት በማገዝ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዴልቦ በበኩላቸው "በመንግስት የቀረበው የአብረን እንስራ ጥያቄ ተገቢና ወቅታዊ ነው" ሲሉ ገልጸውታል።

ወደፊትም የትምህርት ጥራትና አግባብነትን ለማረጋገጥ አገራቸውን በሙያቸው ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን አክለዋል።

መንግስት ከሙያ ማኅበራት ጋር እየተመካከረ ለመስራት ማሰቡ ለትምህርት ጥራት መጓደል ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት ያስችላል ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ሕክምና ማኅበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ተግባር ይግዛው ናቸው።

እርሳቸውና ማኅበራቸውም የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም